ለጤና ተቋማቱ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለጤና ተቋማቱ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
ደብረ ብርሃን (ኢዜአ)መጋቢት 9/ 2014---በሰሜን ሸዋ ዞን በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት 7 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የመድሃኒት እና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
ለጤና ተቋማቱ ድጋፉን ዛሬ ያደረጉት "ምህረት ሜዲካል ሰፕላይ ግሩፕ '' የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እና በሲዳማ ክልል የሚገኙ የግል ጤና ተቋማት ማህበር ናቸው።
'"የምህረት ሜዲካል ሰፕላይ ግሩፕ'' የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ሕይወት ወልዴ በእዚህ ወቅት እንዳሉት፣ በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን የሕክምና ተቋማት መልሶ ለማቋቋም የሁሉም እገዛ ያስፈልጋል።
አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት በሰሜን ሸዋ ዞን ዝርፊያና ጉዳት የደረሰባቸውን የሕክምና ተቋማት ለማቋቋም 6ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ መድኃኒቶችንና የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከችግሩ ስፋት አንፃር የሚያደርጉት ድጋፉ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዳይሬክተሯ ወይዘሮ ሕይወት አረጋግጠዋል።
በሲዳማ ክልል የግል ጤና ተቋማት ማህበር ሊቀመንበር ዶክተር ግርማ አባቢ በበኩላቸው "ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማትን መዝረፍና ማውደም ተገቢነት የለውም" ብለዋል።
ማህበሩ በኤፍራታ ግድምና በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳዎች ለሚገኙ 10 ጤና ተቋማት የሚሰራጩ ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ከድጋፎቹ መካከል ለማዋለጃና ለምርመራ አገልግሎት የሚውሉ 17 አልጋዎች፣ ሁለት የቤተ-ሙከራ መሳሪያዎች እና ሌሎች የሕክምና መሳሪያዎች እንደሚገኙበት ገልፀዋል።
ማህበሩ ካደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ከወረዳዎቹ ለተውጣጡ 35 የጤና ባለሙያዎች የስነ-ልቦና ስልጠና መስጠቱን ተናግረዋል።
ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው ያመለከቱት ዶክተር ግርማ፣ "ችግሮቻችንን በጋራ በመፍታት የጠላቶችን እኩይ ሴራ ማክሸፍ ከሁሉም ይጠበቃል" ብለዋል።
የተደረገው ድጋፍ የዜጎችን ህይወት ለመታደግ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ድጋፉን የተረከቡት የሰሜን ሸዋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ፀዳለ ሰሙንጉስ ናቸው።
'ድጋፉ ለጤና ተቋማቱ በፍጥነት እንደሚደርስ ገልጸው፣ ተቋማቱን መልሶ ለማቋቋም በተለያዩ አካላት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በአሸባሪው ህወሓት የደረሰው ውድመትና ዘረፋ ከፍተኛ በመሆኑ ጤና ተቋማቱን መልሶ የማደራጀት ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ጠቅሰው፤ "ዛሬ የተደረገው ድጋፍ የጎደለውን ለማሟላት ያግዛል" ብለዋል።
በቀጣይ ለኅብረተሰቡ የተሟላ የጤና አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል ድጋፍ የሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።