ቀጥታ፡

ሀገረ ስብከቶቹ ለተፈናቁሉ ወገኖች 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ

ሰቆጣ መጋቢት 9/2014 (ኢዜአ) በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሶስት ሀገረ ስብከቶች ከዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ለተፈናቁሉ ወገኖች በጥሬ ገንዘብና በአይነት 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ድጋፍ አደረጉ።

ከድጋፉ ውስጥ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ብሩ በጥሬ ገንዘብና 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው 300 ኩንታል የዳቦ ዱቄት ደግሞ በአይነት የተደረገ ነው።

ድጋፉን ያስረከቡት በቤተክርስትያኗ የስዊዲንና ስካንዲቢያን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ እንዳሉት ምንም ነገር የማያውቁና ለክፋት ያልቆሙ ህፃናት ለመከራና ችግር ተጋልጦ ማየት ህሊናን ይጎዳል።

"ተጎጂ ወገኖችን በመደገፍ ባጭር ጊዜ የኑሮ ሁኔታቸው እንዲሻሻል በሚቻለው አቅም ሁሉ መጣር ይገባል" ብለዋል።


ከቤት ንብረታችሁ የተፈናቀላችሁ ወገኖች ተስፋ አትቁረጡ አይዟችሁ በማለት ያፅናኑት አቡነ ኤልያስ "ከቤት ንብረታቸው የተፈናቅሉ እናቶችና ህፃናት ከችግራቸው ተላቀው ለማየት ያብቃን" ብለዋል።

በሀገረ ስብከቱ ስር የሚገኙ ምእመናንን በማስተባበር  1 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር ግምት ያለው 300 ኩንታል የዳቦ ዱቄትና በጥሬ ገንዘብ ደግሞ 500 ሽህ ብር ለተፈናቃይ ወገኖች ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ ቀያቸው እስኪመለሱ ምእመናንን በማስተባበር ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

በአሜሪካ አትላንታና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ያዕቆብና በአሜሪካ ኮሎራዶና አካባቢው ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ናትናኤል  በበኩላቸው ለተፈናቃዮች የ600 ሺህ ብር ድጋፍአድርገዋል ።

በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር  አሸባሪው የህውሃት ቡድን በፈፀመው ወረራ የተፈናቀሉ  ከ53 ሺህ በላይ ወገኖች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ  ከአስተዳደሩ የተገኘ መረጃ ያመላክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም