ቀጥታ፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን የተከሰተው ግጭት እየተረጋጋ ነው...የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን

አሶሳ ነሃሴ 28/2010 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ኦዳቢልድግሉ ወረዳ የተከሰተውን ግጭት ለማረጋጋት የጸጥታ ኃይሎች ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ሰይፈዲን ሃሮን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ባለፈው ቅዳሜ ማምሻውን በወረዳው ዳለቲ ቀበሌ ለጊዜው ባልታወቀ ምክንያት ግጭት ተከስቷል። በግጭቱ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ የደረሰው ጥፋትም እየተጣራ መሆኑን ገልጸው ፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ኃይል ከእሁድ ማለዳ ጀምሮ ወደ ስፍራው በመግባት የማረጋጋት ስራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል። የግጭቱ ሁኔታ በአግባቡ ተጣርቶ ለህዝብ በቅርቡ የሚገለጽ ሲሆን ወንጀሉን የፈጸሙ አካላትም ተይዘው ለህግ እንደሚቀርቡ አቶ ሰይፈዲን አስታውቀዋል። ዳለቲ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እብነበረድ በስፋት ከሚመረትባቸው ቀበሌዎች ዋነኛዋ እንደሆነች መረጃዎች ያሳያሉ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም