የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል የእርሻ ልማቱን ከተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ ጋር ማቀናጀት ይገባል

ሀዋሳ ፤ መጋቢት 9/2014 (ኢዜአ) የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻልና የኢኮኖሚ አቅሙን ለማሳደግ የእርሻ ልማትን ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ጋር ማቀናጀት እንደሚገባ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አሳሰቡ ።

ርዕስ መስተዳድሩ በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ  የበጋ ተፋስስ እና የመስኖ ስንዴ ልማት የተካሄደባቸውን አከባቢዎች በመጎብኘት በልማቱ እየተሳተፉ የሚገኙ አርሶ አደሮችን አበረታተዋል።

በወቅቱ ርዕሰመስተዳድሩ ፤ዘንድሮ" የተፈጥሮ  ሀብታችን ለብልጽግናችን"  በሚል በተለየ መንገድ  ወደስራ መገባቱን ገልጸዋል ።

ጉብኝት ያደረጉበት ጉመር ወረዳን ጨምሮ በክልሉ ደጋማ አካባቢዎች ገብስ፣አተር፣ስንዴን ጨምሮ በሌሎችም ቅመማ ቅመምና አትክልት አምራችነታቸው እንደሚታወቁ ጠቅሰው፤ አካባቢው  የመሬት አሲዳማነትና የአፈር መሸርሸር ችግር ያለበት ነው ብለዋል።

አከባቢው የሚታወቅበት ምርት ዘላቂ እንዲሆን የአካባቢ ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ስራ ቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት የተናገሩት አቶ ርስቱ፤ ይህም የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻልና የኢኮኖሚ አቅሙን  ለማሳደግ  ወሳኝ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይ የክልሉን ምርትና ምርታማነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ  የእርሻ ልማትን  ከተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ  ጋር ማቀናጀት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

"በተለይ ማድረግ ይቻላል በሚል ቁጭት ዘንድሮ የጀመርነው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተስፋ ሰጪ ውጤት አሳይቷል" ሲሉ ጠቅሰዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለአርሶ አደሩና የግብርና ባለሙያዎች ለሰሩት ስራ ምስጋና በማቅረብ በቀጣይ ጊዜ ልማቱን በስፋት ለማስፈጸም የሚያስችል አቅም እንዳለ አረጋግጠዋል።

የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን በቀጣይ የመሬቱ ምርታማነት እየጨመረ እንዲሄድ አርሶ አደሩ የግብርና ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር ተግባራዊ ማድረግ  እንዳለበትም ምልዕክት አስተላልፈዋል።

የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል እና የተፈጥሮ ሃብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አንደኛ ሽናሌ ፤ ዘንድሮ በክልሉ በሚገኙ ከ25 ሺህ በላይ ቀበሌዎች ሲካሄድ የቆየው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ በመገባደድ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዘንድሮው በጋ ወራት ለማልማት በተለዩ 3 ሺህ 103  ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ በህዝብ ተሳትፎ መከናወኑን አመልክተዋል።

በአምስት ሳምንታት ውስጥ ከተፈጸሙት ተግባራት መካከል የአፈር ለምነትና እርጥበትን የሚጠብቁ 10 ሺህ 115 ኪሎ ሜትር እርከን ስራ  መከናወኑን የጠቀሱት አቶ አንደኛ፤  2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ህዝብ በልማት ቡድን ተደራጅቶ መሳተፉን አስታውቀዋል።

በጉራጌ ዞን ጉመር ወረዳ የወድበር ቀበሌ አርሶ አደር ደጁ ንጋ በሰጡት አስተያየት፤ በተፋሰስ ልማት ስራው በመሳተፍ የአፈርና ውሃ እቀባ ተግባራት በማከናወን ለግብርና ልማትና እና እንስሳት እርባታ አመቺ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ገልጸው በልማቱ  ጠንክረው እየተሳተፉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"አካባቢያችንን እናልማ፣የውሃና የመሬት ሀብታችንን እንከባከብ፣ያለንን ፀጋ አልምተን እንጠቀም" በሚል መርህ ንቅናቄ ተፈጥሮ የተከናወኑ  ተግባራት ለመመልከት ነው ጉብኝቱ የተዘጋጀው።

በዚህም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣የዞኖች አስተዳደሪዎችና የግብርና ሴክተር  የስራ ሃላፊዎች መሳተፋቸውን ኢዜአ ከሥፍራው ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም