ቀጥታ፡

በህልውና ዘመቻው ወቅት ያበረከትነውን አስተዋጽኦ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ለመድገም ዝግጁ ነን

አዲስ አበባ መጋቢት 09/2014(ኢዜአ) በህልውና ዘመቻው ወቅት ያበረከትነውን አስተዋጽኦ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ለመድገም ዝግጁ ነን ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የግል መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ገለጹ፡፡

የተለያዩ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በተቀናጀ መልኩ የሐሰት መረጃ በማሰራጨት በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ላይ ጫና ሲያሳድሩ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

በአንጻሩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያን በሚመለከት ሲሰራጭ የነበረውን የሐሰት መረጃ ከማጋለጥ ባሻገር ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅ በብርቱ ሰርተዋል፤ እየሰሩም ይገኛሉ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የግል መገናኛ ብዙኃን ተቋማት አመራሮች እንደሚሉት፤ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በህልውና ዘመቻው ወቅት አገር የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ከፍተኛ ሚና አበርክተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው አገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ሰፊ ሽፋን በመስጠት መረጃን ከወዲሁ ተደራሽ  እያደረጉ  መሆኑንም ነው ያነሱት፡፡

የአሃዱ ሬድዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ በኢትዮጵያ አሳታፊ ውይይት፣ ምክክርና መግባባት እንዲካሄድ ለረጅም ዓመታት ሲጠየቅ ቢቆይም ጉዳዩ ባለቤት ሳያገኝ ቆይቷል ይላሉ፡፡

አሁን ላይ ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ ለዓመታት ሲነሳ ለነበረው ጥያቄ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ ተጥሎበታል ብሏል።

አሃዱ ሬድዮና ቴሌቪዥን ከዚህ አኳያ ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮችን በመያዝና ባለድርሻ አካላት ፊትለፊት እንዲወያዩ በማድረግ ዘገባዎችን በተከታታይነት ለአድማጭ ተመልካች  እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአገራዊ ምክክሩ ዙሪያ የሚሰሩ ማናቸውም ዘገባዎች ለምክክሩ ስኬታማነት ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ያለው ጋዜጠኛ ጥበቡ፤ ይህንኑ ሥራ ይበልጥ ለማጠናከር ሚዲያዎች እንደ አንድ ፎረም ሊቋቋሙ ይገባል ብለዋል፡፡  

በአርትስ ቴሌቪዥን የዜና ክፍል ኃላፊ ዳንኤል መኮንን በበኩሉ፤ አርትስ ቲቪ እንደ ሌሎች የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት በህልውና ዘመቻው ወቅት የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ለሚያጎለብቱ ጉዳዮች ሰፊ ሽፋን በመስጠት ስለመስራቱ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ የተቃጣውን የህልውና አደጋ በመቀልበስ ረገድ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

አርትስ ቲቪ አገራዊ ምክክሩ ለአገር ህልውናና በህዝቦች መካከል እየተፈጠሩ ላሉ አለመግባባቶች መፍትሔን እንደሚያመጣ  በጽኑ እንደሚያምን ገልጸው፤ ድርጅቱ ይህን ከግንዛቤ ያስገባ ተግባር እያከናወነ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

አገራዊ ምክክሩን በሚመለከት ምሑራንን፣የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችን፣ፖለቲከኞችንና ሌሎች እንግዶችን በማነጋገር እየሰሩ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

ተቋሙ በቀጣይ አገራዊ ምክክሩን አብይ ጉዳይ አድርጎ እንደሚሰራም ነው ያረጋገጡት፡፡

 የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን(ኢሳት) ሥራ አስፈጻሚ ደረጀ ተክሌ፤ ኢሳት እንደ መገናኛ ብዙኃን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የዜጎችን ድምጽና ሐሳብ ማንጸባረቅ ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የመገናኛ ብዙኃን ህዝብን ለማገልገል በሚያደርጉት ጥረት ላይ አገራዊ ምክክሩን እንደ መልካም አጋጣሚ መጠቀም እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡

በዋናነትም ኮሚሽኑ የሚያሳየውን መንገድ ህዝቡ እንዲከተልና በተቀመጠው አካሄድ መሰረት ሐሳቡን እንዲያቀርብ መገናኛ ብዙኃን ህዝቡን ከማንቃት ጀምሮ በርካታ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡

በዚህ ረገድ ኢሳት ሙያተኞችን በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በማሰማራት በምክክሩ ላይ ግብአት የማሰባሰብ ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፤ በውጭ አገር በሚገኙ ስቱዲዮች የዙም ውይይቶችን እያካሄደ መሆኑንም አንስተዋል።

በቀጣይም ጉዳዩን በሚመለከት በተደራጀ መልኩ ለመሥራት ቡድን ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም