በግንባታ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የጥራት፣የጊዜና በጀት አጠቃቀም ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በግንባታ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የጥራት፣የጊዜና በጀት አጠቃቀም ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተጠቆመ
ሐዋሳ፤ መጋቢት 9/2014(ኢዜአ) በግንባታ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የጥራት፣ የጊዜ፣ የፍጥነትና የበጀት አጠቃቀም ችግሮች እንደሚስተዋሉ ተመላከተ።
በግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ባለፉት ሶስት ዓመታት በታዩ ተግዳሮቶች ዙሪያ የሚመክርና የደቡብ፣ ሲዳማና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በሀዋሳ እየተካሄደ ነው።
በምክክር መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ማተቤ አዲስ እንደገለጹት እንደ ሀገር 60 በመቶ የሚሆነው የካፒታል በጀት ለኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ ይውላል።
"ዘርፉ በተመደበለት በጀት ጊዜና ፍጥነት እንዲጠናቀቅ በማድረግ ኪሳራና ብክነት መከላከል ይገባል" ብለዋል።
ባለስልጣኑ ባለፉት ሶስት ዓመታት የ380 ፕሮጀክቶች የዲዛይን፣ 151 የመንግስት ህንጻ ፕሮጀክቶች፣ 75 በፌዴራል መንግስት የሚከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ 9ሺህ160 የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ብቃት ፍተሻና 758 የዩኒቨርስቲ ፕሮጀክቶች በልዩ ሁኔታ ክትትል መደረጉን አስታውቀዋል።
በዚህም በጥራት፣ በጊዜ፣ ፍጥነትና በበጀት አጠቃቀም ዙሪያ ችግሮች መስተዋላቸውን ጠቁመው ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ አራት ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል።
በመድረኩ የደቡብ፣ ሲዳማና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች የኮንስትራክሽን ቢሮ ሀላፊዎች፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ አመራሮችና በሶስቱ ክልሎች የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተወካዮች እየተሳተፉ መሆኑ ተመላክቷል።