የብልጽግና ፓርቲ በዴሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ ተተኪ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት በማምጣት ተራማጅነቱን በተግባር አሳይቷል - ኢዜአ አማርኛ
የብልጽግና ፓርቲ በዴሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ ተተኪ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት በማምጣት ተራማጅነቱን በተግባር አሳይቷል
አዲስ አበባ ፣መጋቢት 09/2014 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ በዴሞክራሲያዊና ነጻ ምርጫ ተተኪ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት በማምጣት ተራማጅነቱን በተግባር አሳይቷል ሲሉ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተናገሩ፡፡
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ምርጫ ሂደት አሳታፊና ትክክለኛ ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት የተረጋገጠበት እንደነበርም ነው ያነሱት፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ከሰሞኑን በአዲስ አበባ ባካሄደው የመጀመሪያ ጉባኤው የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎ መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
በጉባኤው የፓርቲውን ፕሬዝዳንት ጨምሮ ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶችን እንዲሁም የማዕከላዊና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተመረጡ ሲሆን፤ የምርጫ ሂደቱም ለኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ ተላልፏል፡፡
በዚህም ፓርቲው በርካታ ተተኪ አመራሮችን ወደ ኃላፊነት አምጥቷል፡፡
በጉባኤው የተካሄደውን ምርጫ አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንደሚሉት፤ ጉባኤው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አዲስ ዴሞክራሲያዊ ልምምድ የታየበት ነው፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ግርማ የሺጥላ፤ በጉባኤው አንዱ ተመልካች ሌላኛው ደግሞ ወሳኝ ሳይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ያለምንም ገደብ የፈለጉትን አካል መርጠዋል ብለዋል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎች በብሔርና ክልል አጥር ሳይገደቡ ትክክለኛ ህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትን በተግባር ማሳየታቸውንም ነው ያነሱት፡፡
ሌላኛዋ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ በበኩላቸው፤ በጉባኤው የተካሄደው ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊና ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አርአያ የሚሆን ጭምር ነው ብለዋል፡፡
ጉባኤው አሳታፊ ከመሆኑም ባሻገር ለኢትዮጵያ ህዝብ በቀጥታ የተላለፈ መሆኑን በማስታወስ፤ ይህም ብልጽግና በኢትዮጵያ ሊያሳካው ለሚፈልገው አሳታፊ የዴሞክራሲ ስርዓት መሰረት የጣለ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲያዊነትን በተግባር በማሳየት በኢትዮጵያ የሰለጠነ የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፍን አርአያ መሆኑንም ተናግረዋል።
ፓርቲው ከምስረታው ጀምሮ በአመራር ግንባታ ላይ ያተኮሩ ተግባራትን እያከናወነ መምጣቱን በመጥቀስ፤ በጉባኤው ተተኪ ወጣት አመራሮችን ወደ ኃላፊነት በማምጣት ተራማጅነቱን አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
ፓርቲው አዲሱን ትውልድ ልምድ ካለው ጋር በማጣመር ወደ ተሻለ ነገ ሊያሻግር የሚችል ጠንካራ የአመራር መስተጋብር መፍጠሩንም አንስተዋል፡፡
የአፈጻጸምና የስነ-ምግባር ችግር ያለባቸው አመራሮች ላይ ርምጃ በመውሰድም ለህግ የበላይነት መስፈን ያለውን ቁርጠኝነት ማሳየቱንም እንዲሁ፡፡
አመራሮቹ አክለውም ፓርቲው በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ የተቀመጡ የአቋም መግለጫዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ኀብረተሰቡን በማስተባበር እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
በየደረጃው ያሉ የፓርቲው አመራሮች በአቋም መግለጫው የተነሱ ሃሳቦችን እውን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ነው የገለጹት፡፡
መላ ኢትዮጵያዊያን የብልጽግና ፓርቲ ሌብነትን የሚፀየፍ አገልጋይ አመራር በመፍጠር ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን በሚያደርገው ጥረት ላይ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የብልጽግና ፓርቲ ኀብረተሰቡን በማሳተፍ የተሻለች ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡