መገናኛ ብዙሃን ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት አዎንታዊ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት አዎንታዊ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል
መጋቢት 08 ቀን 2014(ኢዜአ) መገናኛ ብዙሃን ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት አዎንታዊ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።
በመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን እና በመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት አዘጋጅነት ዓመታዊው የሚድያና የኮሙኒኬሽን ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል።
ጉባኤው "እውነተኛ መረጃ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተከናወነው።
መድረኩ መገናኛ ብዙሃን በቀጣይ ለሚመጡ ሁነቶች ከወዲሁ ዝግጅት እንዲያደርጉና ባለፉት ጊዜያት ከተፈጠሩ ችግሮች ትምህርት እንዲወስዱ ለማስቻል መዘጋጀቱ ተመላክቷል።
እንዲሁም መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩ ለማስቻል እንደሆነም ተገልጿል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በነበረው ህግ የማስከበር እርምጃ የውጭ መገናኛ ብዙሃን የዘገባ ትርክቶች እና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ ሁነቶች ላይ የነበራቸውን ሚና በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በዚህም የውጭ መገናኛ ብዙሃን በርካታ የሀሰት መረጃዎችን ሲያስተጋቡ እንደነበር እና በአንጻሩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ትክክለኛ መረጃ ተደራሽ ማድረጋቸውን ተመላክቷል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ መገናኛ ብዙሃን ለአገር ግንባታ እያደረጉት ላሉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
መገናኛ ብዙሃን በስራዎቻቸው ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎችን እንዲያከናውኑና የሀሰት መረጃዎችን በመመከት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
በቀጣይ የሚከናወነው ብሔራዊ ምክክር የተሳካ እንዲሆን መገናኛ ብዙሃን አውንታዊ ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚንስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው መገናኛ ብዙሃን ስብራቶችን በመጠገን በኩል ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ብለዋል።
በተለይም ጽንፈኝነትን እና አግላይነትን በማከም በኩል ባለፉት አራት ዓመታት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እየተወጡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
መገናኛ ብዙሃን ለህዝቡ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ማጠናከር አለባቸው ያሉት ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ናቸው።
በሀገር ግንባታ ሂደት የህብረተሰቡን ተሳትፎ ሊያጎለብቱ የሚችሉ ስራዎች መስራት እንደሚጠበቅባቸውም እንዲሁ።
በጉባኤው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሁም የሲቪክ ተቋማት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡