ቀጥታ፡

ጠንካራ አንድነት እንዲገነባ ሁሉም ዜጋ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በንቃት መሳተፍ ይጠበቅበታል

ሀዋሳ፣  መጋቢት 8/2014 (ኢዜአ) ጠንካራ አንድነት እንዲገነባ ሁሉም ዜጋ ለሀገራዊ ምክክሩ መሳካት በንቃት በመሳተፍ የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የስነ- ልቦና ምሁራን ተናገሩ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች  መደማመጥና የሚጠበቅባቸውን ድርሻ በመውሰድ ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።

ያለፈውን በመተው የወደፊት ተስፋን የማየት አዎንታዊ አመለካከትን መነሻ ያደረገ ተሳትፎ ማድረግ  ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ እንደሆነ ነው ምሁራኑ ያመለከቱት።

በዩኒቨርሲቲው የስነ-ልቦና መምህርት ማህሌት አሸናፊ፤  በሀገራችን በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ ግጭቶችና የሰላም እጦቶች ያስከተሏቸው የስነ-ልቦና ጉዳቶችን ለማከም ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ዘመን የተሻገሩ ቁርሾዎችን በማስወገድ የጋራ መግባባትን በማጠናከር የአብሮነት እሴት ለማስቀጠል ያለው ሚና የላቀ መሆኑን ገልጸው፤ ጠንካራ አንድነት እንዲገነባ ሁሉም ዜጋ ለምክክሩ ስኬታማነት በንቃትና በቀናነት መሳተፍ  እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

ሁሉም ሀላፊነቱን ከተወጣ ምክክሩ የስነ ልቦና ስብራቶችን በመጠገንና የነበሩ ስህተቶችን በማረም ወደ አዲስ ምዕራፍ የማሻገር አቅም እንደሚኖረው አስረድተዋል።

"ግጭቶች ተፈጥሮዊ በመሆናቸው ካለግጭት መኖር አይቻልም፤ ግጭቶችን የምንይዝበት፣ ወደ መደበኛው ሁኔታ የምንመልስበትና ሰላምን የምንገነባበት መንገድ ማፈላለግ ተገቢ ነው "ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በኢትዮጵያ እንደ የማህበረሰብ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ምሳሌ መሆን የሚችል ሰላም ማውረጃ እሴቶች ያሉ  በመሆኑ ይህንን ለምክክሩ መጠቀም እንደሚበጅም ጠቅሰዋል።

መምህርት ማህሌት  "በኦሮሞ የገዳ፣ በሲዳማ የአፊኒ፣ በጋሞ እግንሶ" የሚባሉ  አለመግባባቶችን መፍቻና ዘላቂ ሰላም መገንቢያ እሴቶችን መጠቀም ይገባል ሲሉ አመላክተዋል።

ለዚህ ደግሞ በየአካባቢው የሚገኙ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች፣ የፖለቲካ መሪዎችና የሲቪል ማህበረሰብ አባላት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

መላው ማህበረሰብ ምክክሩ ስኬታማ ሆኖ ጠንካራ አንድነት እንዲገነባና የተፈለገውን ግብ እንዲመታ በንቃት መሳተፍ ይጠበቅበታል ሲሉ አብራርተዋል።

ሀገሪቱ ያለፈቻቸው የፖለቲካ ስርዓት አለመብሰልና ሀገር በቀል ማንነት ያለመላበስ ምክንያት የተከሰቱ ግጭቶችና አንዱ በአንዱ ላይ የበላይነትን ለመውሰድ የፈጠሯቸው ጠባሳዎች ለነገ ህይወት እንቅፋት ናቸው ያሉት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲው የስነ- ልቦና መምህር ሀብተማሪያም ካሳ ናቸው።

ማንም ለብቻው መኖር የማይችል በመሆኑ እንዲህ ዓይነት የሰውን የማሰብና የድርጊት ችሎታን የሚገቱ ቂምና ቁርሾ ለማምከን ደግሞ ውይይትና መመካከር ብቸኛ መንገድ መሆናቸውን አንስተዋል።

በምክክሩ ላይ አንዱ ለሌላው አስፈላጊ መሆኑን  በመረዳት በቀናነትና በርህራሄ ስሜት የሞራል ልዕልና ባለው መልኩ መከወን እንደሚገባ አመልክተዋል።

በአንዱ ማደግና መበልጸግ ውስጥ ሌላው እንዳለ ማሰብ እንጂ ብቻውን ማንም ምንም እንዳላመጣ ማወቅና መገናዘብ ተገቢ ነው፤  በዚሁ ልክ በሀገራችን በተፈጠሩ በሁሉም ችግሮች ውስጥ የሁሉም ድርሻ እንዳለው ማወቅ ተገቢ ነው ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሃይማኖት አባቶችና ሌሎች ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን መደማመጥና የእኔ ድርሻ ምን ነበር አሁንስ ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል ማለት ይገባል ነው ያሉት ምሁሩ።

የሁሉም የመጨረሻ ግብ የተሻለ ህይወት ማምጣት በመሆኑ ለአብሮነትና ለመተጋገዝ በሚያስችል መልኩ ምክክሩን በማካሄድ ኢትዮጵያን  ወደ ጥሩ ጎዳና ማምጣት ይገባናል ብለዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባት ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅና ኮሚሽኑን የሚመሩ የ11 ኮሚሽነሮች  ሹመት ማጽደቁ  ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም