የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በሰላም ግንባታ ሂደት ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በሰላም ግንባታ ሂደት ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል
አዳማ፣ መጋቢት 08/2014(ኢዜአ) የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች በሰላም እሴት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት እንደሚገባቸው የሰላም ሚኒስቴር አመለከተ።
ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ አባገዳዎችና ሃዳ ሲንቄዎችን እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችን ያሳተፈና "ፌዴራልዝምና የሰላም እሴት ግንባታ በኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ ውይይት ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።
በሰላም ሚኒስቴር የፌዴራሊዝምና ግጭት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ስዩም መስፍን በውይይቱ ላይ እንደገለፁት ኢትዮጵያ የመቻቻልና የአብሮ መኖር እሴቶች መገለጫ ሀገር ናት።
በተለይም የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ግጭትን የሚፈቱበትና የሚይዙበት ባህል ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
"ይሁንና ባለፉት አራት ዓመታት የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ባህላዊ የግጭት አፈታት ሚና እጅጉን አናሳ ነበር" ያሉት ዶክተር ስዩም፤ "በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ራሳቸው የችግሩ ባለቤት የሆኑበት ሁኔታም ታይቷል" ብለዋል ።
መድረኩ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች አሁን ላይ ከሚስተዋሉ የጎጠኝነትና መንደርተኝነት አስተሳሰብ ነጻ ሆነው በቱባ የግጭት አፈታት ባህልና የሰላም እሴቶች ግንባታ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ መሆኑን አመልክተዋል ።
"ለዚህም ሊኖር የሚችለውን የአመለካከት፣ የግንዛቤ ክፍተቶችና የአስተሳሰብ መዛነፎችን ለመቅረፍ የማሰልጠኛ ማኑዋሎች ተዘጋጅተዋል" ብለዋል።
"ሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ሀገሪቱን አሁን ካለችበት ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ለማላቀቅ በግጭት አፈታት፣ በአስተዳደርና አስተማማኝ ሰላም መስፈን የነቃ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይገባል" ሲሉ አመልክተዋል ።
በየአካባቢው ያለውን የግጭት አፈታት ባህል በመጠቀም አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።
የፌዴራልዝም ስርዓት ጽንሰ ሐሳብ "ግጭትን በመቀነስ፣ አብሮ መኖርና በጋራ መልማት ነው" ያሉት ደግሞ በኢዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የአንትሮፖሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ደሳለኝ አምሳሉ ናቸው።
ህብረ ብሔራዊ ፌዴራልዝምን በአግባቡ መምራትና ማስተዳደር ከቻልን ለሀገር አንድነት፣ ለእኩልነትና ለፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ብሎም ለጋራ ልማትና ዕድገት ጥሩ አማራጭ መሆኑን ጠቁመዋል።
ነገር ግን በአግባቡ ማስተዳደርና መያዝ ካልተቻለ በተቃራኒው ለቡድኖች ሀብት መሰብሰቢያና ለስልጣን ማራዘሚያ በመሆን የግጭት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።
የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎችም በባህላዊ እሴቶቻችን ልክ እየተጫወቱ ያለው ሚና አናሳ በመሆኑ ለግጭቶች መበራከት አይነተኛ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ባህላዊ የግጭት አፈታት እሴቶች እንዲጎለብቱና በሰላም ግንባታ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና እንዲኖራቸው ለማስቻል በትኩረት መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።