ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የቀጣናውን አገራት የመሰረተ ልማት ትስስር በማጠናከር የምጣኔ ሃብት እድገት እንዲፋጠን እየሰራች ነው

መጋቢት 8/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የቀጣናውን አገራት የመሰረተ ልማት ትስስር በማጠናከር የምጣኔ ሃብት እድገት እንዲፋጠን እየሰራች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በሳምንታዊ መግለጫቸው በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፤ ቀጣናዊ ትብብርና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ በማተኮር ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዲፕሎማሲው ዙሪያ የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሹ ቢንግ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸውን ለአብነት አንስተዋል።

የኢትዮጵያን ሰላም ለማስጠበቅ ሁሉንም የሚያሳትፍ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና ለስኬቱም እስረኞች መፈታታቸውን አቶ ደመቀ አስረድተዋል፡፡

ከሱዳን ጋር በድንበርና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሰላማዊ የመፍትሄ አማራጭ መትከል የመንግስት ፍላጎት እንደሆነም ገለፃ መደረጉን ተናግረዋል።

የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ልዑካንም የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ለሰላም፣ ለመልካም አስተዳደርና ለልማት ተባብረው እንዲሰሩ ቻይና ጽኑ ፍላጎት እንዳላት መግለፃቸውን ጠቁመዋል።

የቀጣናው ሀገራት በባቡርና ሌሎች መሰረተ ልማቶች በመተሳሰር ምጣኔ ሃብታዊ እድገት እንዲያስመዘግቡ የኢትዮጵያ ሚና ጉልህ እንደሆነ መጠቀሱንም አብራርተዋል።

በዚህ ሂደትም ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የመልሶ ግንባታና ሌሎች የልማት ስራዎች የቻይና ድጋፍ እንደማይለያት መገለጹን አንስተዋል።

የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት ሁሉን አቀፍና ስትራቴጂካዊ አጋርነት የተንጸባረቀበት ስለመሆኑም በውይይቱ የተነሳ ሲሆን ቻይና ለኢትዮጵያ ላበረከተችው ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ምስጋና ቀርቧል።

በቅርቡ አዲስ ለተሾሙ አምባሳደሮች በጃፓን፣ አሜሪካ፣ ግብጽ ፓኪስታንና ሌሎች ሀገራትም የስራ ስምሪት መሰጠቱን አስታውሰዋል።

በአልጀሪያና በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ከኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን ምርቶች ማስተዋወቅ መቻላቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያዊያን ወዳጆች ከኤርትራዊያን ጋር በመተባበር HR-6600 በመቃወም በአሜሪካ ሰልፍ ማካሄዳቸውንም ጠቅሰዋል።

በሳዑዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ከ100 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው የማስመለስ ስራ መጠናቀቁንና 35 ሺህ የሚሆኑት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለመልሶ ግንባታ የሚውል 110 ሺህ የደቡብ አፍሪካ ራንድ ማሰባሰባቸውን ጠቁሟል።

በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ደህንነት ለማስጠበቅም ከአገሪቱ የኢሚግሬሽንና ደህንነት ኃላፊዎች ጋር ውይይት መካሄዱ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም