ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር ሃይል አጠቃላይ ዝግጁነትና አሁን ያለበት ቁመና አስደስቶናል

መጋቢት 7 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር ሃይል አጠቃላይ ዝግጁነትና አሁን ያለበት ቁመና አስደስቶናል፤ኩራትም ተሰምቶናል ሲሉ በቢሾፍቱ አየር ሃይል ጉብኝት ያደረጉ የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦች ገለጹ።

የኢትዮጵያ የምንጊዜም ጀግናዋን አትሌት ደራርቱ ቱሉ ጨምሮ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ እና ሌሎችም ታዋቂ ሰዎች በቢሾፍቱ የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው በተመለከቱት የኢትዮጵያ አየር ሃይል አጠቃላይ ዝግጁነትና ያለበት ቁመና አስደስቶናል፤ኩራትም ተሰምቶናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ አየር ሃይል በነበረኝ ጉብኝት በተመለከትኩት ሁሉ ደስታና ኩራት ተሰምቶኛል ስትል ጀግናዋ አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ገልፃለች።

የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከዘመኑ ጋር ዘምኖ የአገር አለኝታ እንዲሆን ላደረጉ ሁሉ ታላቅ አክብሮትና ምስጋና ይገባቸዋልም ብላለች።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ፤ የኢትዮጵያ አየር ሃይልን ለመጀመሪያ ጊዜ መጎብኘቱን ገልፆ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ምን ጊዜም የአገር ኩራት መሆኑን በተግባር ተመልክቻለሁ ብሏል።

ከዚህ በፊት ለመግባት ይቅርና በውጭ እንኳን በአይን ለማየት ይከለከል የነበረን ቦታ ገብቶ በማየቱ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረለትም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ አየር ሃይልን የመሰለ ዘመናዊ ተቋም ለህዝብ ክፍት ሆኖ ማየት መቻል የኔነት ስሜት ከመፍጠሩ በላይ ደስታና ኩራቱ ከፍተኛ መሆኑንም ገልጿል።

የአዲስ አበባ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ዮናስ ዘውዴ፤ በጉብኝታቸው አየር ሃይል የነገይቷን ኢትዮጵያ አመላካችና አለኝታ መሆኑን በቅጡ ተረድቻለሁ ብለዋል።

በጉብኝቱ ላይ የተገኘው አርቲስት አብራር አብዶ በበኩሉ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከዚህ ቀደም ከሚያውቀው በእጅጉ የተደራጀና የዘመነ ሆኖ በማግኘቱ መደነቁን ገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር ሃይል የአገር መከታና የትውልዱ መሰረት ሆኖ እንደሚቀጥል በተመለከትነው ሁሉ አረጋግጠናል ብሏል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም