ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጃካርታ በረራ ሊጀምር ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2010 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኢንዶኔዥያ ጃካርታ በረራ ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። በረራው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከሐምሌ 17 ቀን 2018 ጀምሮ በሳምንት ሶሰት ቀናት እንደሚካሄድ አየር መንገዱ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል። በኢንዱስትሪ አመርቂ ዕድገት እያስመዘገቡ የሚገኙ አገራት ስብስብ የሆነው የቡድን 20 አባል ኢንዶኔዥያ በህዝብ ብዛት ከዓለም አራተኛ ስትሆን በምጣኔ ኃብትም ገንዘባቸው ከፍተኛ የመግዛት አቅም ካላቸው የዓለም አገራት በ10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። አዲስ የሚጀመረው የጃካርታ በረራም አየር መንገዱ በዓለም ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ወዳላቸው ሌሎች አምስት የአካባቢው አገራት መዳረሻ እንዲኖረው የሚያስችለው መሆኑም ተመልክቷል። የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እንደተናገሩት አዲሱ የበረራ መስመር አየር መንገዱ አገልግሎቱን በኢሲያ ለማጠናከር የሚያስችለው ከመሆኑም በላይ አዲስ አበባን የመዳረሻ ማዕከል በማድረግ ለፀሎት ጉዞና ለምእራብ አፍሪካ ማህበረሰብ አማራጭ የጉዞ መስመር ይፈጥራል። ይህም በኢትዮጵያ ቱሪዝም፣ ንግድና የህዝብ ለህዝብ ትስስር እንዲጎለብት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ገልጸዋል። አየር መንገዱ የአፍሪካ አህጉርን ጠንካራ የንግድ ማእከላት ከሆኑ የዓለም ክፍሎች ጋር ለማገናኘት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አቶ ተወልደ ተናግረዋል። የስታር አሊያንስ አባልና የ96 አውሮፕላኖች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አህጉራት 110 መዳረሻዎች አሉት።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም