ተጠያቂነትን በማስፈን የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦትን ለማሻሻል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ተጠያቂነትን በማስፈን የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦትን ለማሻሻል እየተሰራ ነው
ሀዋሳ፤ መጋቢት 07/2014 (ኢዜአ) ተጠያቂነትን በማስፈን የመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት የበለጠ ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ሶስተኛ ምዕራፍ ማስጀመሪያ መድረክ በሲዳማ ክልል ይርጋለም ከተማ ሲካሄድ እንደተመለከተው፤ መሰረታዊ አገልግሎቶች ለማሻሻል የሚደረገው ስራ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚያከናወን ነው ፡፡
በገንዘብ ሚኒስቴር የማህበራዊ ተጠያቂነት ባለሙያው አቶ አበበ ካሳ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በትምህርት፣ግብርና፣ ጤና፣ ውሃና የመንገድ ስራዎች ላይ የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም ባንክ ባገኘው ገንዘብ ድጋፍ ላለፉት አስር ዓመታት በሃገሪቱ በተመረጡ 416 ወረዳዎች የማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ተዘርግቶ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች አማካይነት ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል።
በነዚህ ዓመታት የማህበረሰቡን ግንዛቤ የሚያሳድጉ የተለያዩ መድረኮችን በማዘጋጀት መሰረታዊ አገልግሎቶችን ጥራት ማሻሻል የሚያስችሉ ስራዎችን መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡
ህዝቡ የሚያነሳቸውን የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ በተለይም አካል ጉዳተኞች፣ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች ወጣቶችና ሴቶች ድምጻቸውን የሚያሰሙበትና መንግስትም ምላሽ የሚሰጥበት መድረኮችም እንዲሁ፡፡
የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ ማህበራዊ አገልሎቱን በማሻሻል ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ነው ያሉት ባለሙያው፤ በመንግስትና በዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት መልካም በማድረግ ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡
ፕሮግራሙ ብልሹ አሰራሮችን በማስወገድ ጥራት ያለውን አገልግሎት ለዜጎች የማድረስ ሂደቱን የሚያግዝ በመሆኑ ስራውን ከበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ ተረክቦ ተቋማዊ የማድረግ ስራ በዘንድሮ ዓመት እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡
ለዚህም 20 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ከአለም ባንክ ድጋፍ መገኘቱን ገልጸው፤ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት እንደሚተገበር ነው የተመለከተው።
በዚህም በመጀመሪያው ምዕራፍ ከ416 ወረዳዎች ውስጥ ስልሳዎቹን መንግስት ተረክቦ ተቋማዊ አሰራር እንደሚዘረጋላቸው ተናግረዋል፡፡
በተመረጡ ወረዳዎች ያሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በመሰረታዊ አገልግሎት ላይ ከእቅድ ጀምሮ ዜጎችን አሳታፊ እንዲያደርጉ የሚያስችል አሰራር ይዘረጋል ብለዋል አቶ አበበ።
በኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም የአቅም ግንባታ ባለሙያ ወይዘሮ የሺእመቤት አይኔ በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ በመሰረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ላይ ተጠያቂነትን በማስፈን አገልግሎቱ እንዲሻሻል የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ መንግስትና በአለም ባንክ ስምምነት በተለያዩ በጎ አድራጊ ማህበራት እየተሰራ ሶስተኛ ምእራፍ ላይ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
በሲዳማ ክልል የሚገኙ ስምንት ወረዳዎች ላይ ፕሮግራሙ መተግበሩን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አራርሶ ገረመው ናቸው፡፡
መንግስት በሚያከናውነው መሰረታዊ አገልግሎቶች ላይ ማህበረሰቡ ባለቤት ሆኖ እንዲነጋገርበትና የድርሻውን እንዲወጣም እድል የፈጠረ ፕሮግራም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በየቀበሌው የማህበራዊ ተጠያቂነት ኮሚቴ በማቋቋም ፕሮግራሙን ውጤታማ ለማድረግ በተሰራ ስራ ሞጋች ማህበረሰብ መፈጠሩን የገለጹት ሃላፊው፤ ቅድሚያ የሚያስፈልገውን አገልግሎት እስከመለየት የተደረሱ ስራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
ከፕሮግራሙ ተጠቃሚ አካባቢዎች መካከል የጎርቼ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጻዲቁ ባጢሶ፤ ወረዳው በሁለት ምዕራፎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸው የማህበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት የሚያቀርባቸውን መሰረታዊ አገልግሎቶችን አሰራር ከማሻሻል ባለፈ ማህበረሰቡ ከ7 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ጠረጋ ስራ በማከናወን መንግስት ጠጠር እንዲያለብስለት በማድረግ ለአገልግሎት ማብቃቱን ጠቅሰዋል፡፡
በመድረኩ ከፌደራልና ከሲዳማ ክልል ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡