ቀጥታ፡

የበጎ ፍቃደኛ ከያኒያን ያገኙት ክህሎት በሚፈልጉት ሙያ ለመሰማራት አቅም እንደፈጠረላቸው ወጣት ሰልጣኞች ገለፁ

አዲስ አበባ ነሃሴ 28/2010 የኢትዮጵያ ብሄራዊ የባህል ማዕከል ከበጎ-ፍቃደኛ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በተለያዩ የጥበብ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 139 ታዳጊዎችና ወጣቶች ዛሬ አስመረቀ። ታዳጊዎቹና ወጣቶቹ በክረምት የበጎ ፍቃድ መርሃ ግብር አማካኝነት የሰለጠኑት በባህላዊ ውዝዋዜ፣ በስነ ፅሁፍና በቲአትር  የኪነ ጥበብ ዘርፎች ነው። በመርሃ-ግብሩ ሰባት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በበጎ ፍቃደኝነት በአሰልጣኝነት ተሳትፈዋል። ተመራቂዎቹ ለኢዜአ እንደገለጹት ስልጠናው ስለ ባህላዊ ውዝዋዜና ስነ ዕሁፍ እንዲሁም ትያትር ዕውቀት እንዲኖራቸው ከማገዝ ባለፈ በቀጣይ ወደ ሙያው ለመሰማራት ጉልህ ሚና ይኖረዋል። ስልጠናው በሚወዱት የኪነ ጥበብ ዘርፍ ክህሎት እንዲጨብጡ ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት መስክ የመሰማራት ፍላጎትም አሳድሮባቸዋል። በባህላዊ ውዝዋዜ የሰለጠኑት ዮርዳኖስ ተገኝ፣ ናርዶስ ጥላሁን እና ተስፋ ታምራት እንደተናገሩት ስልጠናው በቀጣይ በባህላዊ ውዝዋዜ ዘርፍ ለመሰማራት ያላቸውን ፍላጎት የሚያሰፋው መሆኑንም ተናግረዋል። ከስልጠናው ያገኙትን ዕውቀትም ለሌሎች ባልንጀሮቻቸው የማካፈል ፍላጎት እንደፈጠረላቸውም ገልጸዋል። በስነ-ፅሁፍና ቲአትር የሰለጠኑት ሚካኤል ስዩምና ቅድስት የኋላ እሸት በሰጡት አስተያየት ደግሞ አንጋፋ  ከሆኑ ከያኒያን የቀሰሙት የሙያ ክህሎት ብቻ ሳይሆን ጠንክሮ የመስራ ባህልንም ጭምር መሆኑን ይናገራሉ። ይህንንም ተሞክሮ በመውሰድ ከፍ ወዳለ ደረጃ መድረስ እንደሚፈልጉና የተማሩትን ዕውቀትና ልምድ ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ገልፀዋል። በዘንድሮው ክረምት ወጣት ተማሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ዘርፎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸው ይታወቃል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም