ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የአመጋገብ መመሪያ ይፋ ሆነ

መጋቢት 6/2014 (ኢዜአ) የጤና ሚኒስቴርና ሌሎች ተቋማት በጋራ ለአራት ዓመታት ያዘጋጁት በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የአመጋገብ መመሪያ ይፋ ሆነ።

የአመጋገብ መመሪያውን የጤና ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ሌሎች አጋር አካላት በጋራ ያዘጋጁት መሆኑም ታውቋል።

በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሰዎችን ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነት በመጨመር ለሞትና የአካል ጉዳት የሚዳርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የአመጋገብ ሥርዓትን ለማሻሻል የዜጎችን የገቢ መጠን ያገናዘበ በንጥረ ነገሮች የበለጸጉ ምግቦችን የመመገብ ልምድ መተግበር ይገባል ብለዋል፡፡

የአመጋገብ መመሪያው ኢትዮጵያ በምግብና ምግብ ስትራቴጂ ያስቀመጠቻቸውን ቁልፍ ጉዳዮች ገቢራዊ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከአመጋገብ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል መመሪያው አጋዥ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ቶሌራ፤ የአመጋገብ መመሪያው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ የሚከሰትን የህፃናት መቀንጨርና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ተጋላጭነታቸውን ይቀንሳል ብለዋል፡፡

የአመጋገብ መመሪያው ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን የህብረተሰብ ጤና፣ የሥርዓተ ምግብ፣ የምግብ ምርትና ምርታማነትን እንዲሁም የማህበረሰቡን የአመጋገብ ዘይቤ ለማስተካከል ያግዛል ነው ያሉት።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ብርሀኑ ነጋ፤ በኢትዮጵያ የምግብ አማራጮችን መሰረት ያደረገ የአመጋገብ ሥርዓት የተለመደ ባለመሆኑ በተማሪዎች ውጤታማነት ላይ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አንስተዋል።

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የትምህርት ቤት ምገባ መርሃግብር እንዲስፋፋ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ምግብን መሰረት ያደረገ የስነ-አመጋገብ ሥርዓት ትምህርት ሚኒስቴር ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ በማካተት አገር አቀፍ የአመጋገብ ባህልን ለማሻሻል ይሰራልም ነው ያሉት።

አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ ለምርት የሚሆን የእርሻ ቦታ እንዲኖራቸውና ተማሪዎችን ዘመናዊ ግብርና ለማስተማር ታስቧልም ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ፤ የግብርና ባለሙያዎችን በማሳተፍ አርሶ አደሩን እና ከፊል አርብቶ አደሩን በአመራረትና አመጋገብ  ዙሪያ ትምህርት ለመስጠት የአመጋገብ መመሪያው ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ኤክስቴንሽን ሥርዓቱን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ መነሻ የሚያገለግል ሰነድ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በዓለም ላይ ከ100 በላይ አገሮች ምግብን መሰረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያ ያላቸው ቢሆንም ከእነዚህ አገራት መካከል የአፍሪካ አገሮች ሰባት ብቻ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም