የኢዜአ 80ኛ አመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት በኦሮሚያ ደረጃ የተዘጋጀ የፎቶ እና ቪዲዮ አውደ ርእይ ነገ ክፍት ይሆናል - ኢዜአ አማርኛ
የኢዜአ 80ኛ አመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት በኦሮሚያ ደረጃ የተዘጋጀ የፎቶ እና ቪዲዮ አውደ ርእይ ነገ ክፍት ይሆናል
አዳማ፤ መጋቢት 6/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት 80ኛ አመት የምስረታ በዓልን በማስመልከት በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የተዘጋጀ የፎቶ እና ቪዲዮ አውደ ርእይ ነገ በአዳማ ከተማ ይከፈታል።
የኢዜአ የህዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ዮሀንስ ወንድይራድ እንደገለጹት አውደ ርእዩ ኢዜአ በሀገር ግንባታ ውስጥ ላለፉት 80 አመታት የነበረውን ሚና የሚያሳይና ተቋሙ በቀጣይ ከየት ወደ የት የሚለውን የሚያመላክት ነው።
በአውደ ርእዩ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የአዳማ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሳተፉ አመልክተዋል።
በተጨማሪም ኢዜአ ባለፉት 80 አመታት በሀገር ግንባታ፣ አስተማማኝ የዜና ምንጭ በመሆን ለመገናኛ ብዙሀን ትክክለኛ መረጃ በማቀበልና በቀጣይ በሚኖረው ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
አውደ ርእዩ ከኦሮሚያ ብሮድ ካስት ኔት ወርክ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ክፍት እንደሚሆን ታውቋል።