ቀጥታ፡

በአገራዊ የምክክር ሂደቱ ለአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና የመረጃ ተደራሽነት ትኩረት ማድረግ ይገባል

መጋቢት 6/2014 (ኢዜአ) በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ለአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና የመረጃ ተደራሽነት የብሬል ዝግጅትና የምልክት ቋንቋ ትኩረት እንዲደረግበት አካል ጉዳተኞች ጠየቁ።

የኢትዮጵያ አካልጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ባዘጋጀው መድረክ ለአገራዊ ምክክሩ የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎ ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደርጓል።

በኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ 11 ኮሚሽነሮች ተሰይመውለት ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ምክክር ለማድረግ በሂደት ላይ ይገኛል።

በመሆኑም በዚህ ምክክር ላይ የአካል ጉዳተኞች የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት የተውጣጡ ዜጎች ውይይት አድርገዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ሲሳይ ሰማኸኝ፤ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ድጋፍ ያልታከለበት አገራዊ ጉዳይ ውጤት ሊያመጣ ስለማይችል በአገራዊ ምክክሩም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ለአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና የመረጃ ተደራሽነት በተለይም የብሬል ዝግጅትና የምልክት ቋንቋ ታሳቢ ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ሙሴ ጥላሁን በበኩላቸው፤ አካል ጉዳተኞች ለምክክሩ ከተሳትፎም ባለፈ የራሳቸውን አበርክቶ ጨምረው ታሪካዊ አሻራቸውን ማሳረፍ አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ፤ በአገራዊ ምክክሩ አካል ጉዳተኞች የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ፌዴሬሽኑ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ዶክተር ሄኖክ ስዩም፤ አገራዊ ምክክሩ አካታችና ሁሉንም አሳታፊ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም አካል ጉዳተኞች በምክክሩ ተሳትፎና እገዛቸው ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም