በአየር ንብረትና በአከባቢ ላይ ተፅጽዕኖ የማያሳድሩ የፈጠራ ሥራዎችን የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በአየር ንብረትና በአከባቢ ላይ ተፅጽዕኖ የማያሳድሩ የፈጠራ ሥራዎችን የሚደግፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
መጋቢት 6/2014 (ኢዜአ) በአየር ንብረትና በአከባቢ ላይ ተፅጽዕኖ የማያሳድሩ የፈጠራ ሥራዎችን (የአረንጓዴ ሥራ ፈጣሪነት) ለመደገፍ የሚውል የአንድ ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክተ ይፋ ተደረገ።
ፕሮጀክቱ ሪች ፎር ቼንጅና አይኪያ ፋውንዴሽን በተሰኙ ግብረሰናይ ድርጅቶ በሁለም የአገሪቱ አከባቢዎች ለአንድ ዓመት ተኩል ተግባራዊ ይደረጋል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ 360 ለሚደርሱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በዘርፉ ሥራ ለመፍጠር የሚያስችላቸውን የሥልጠና ድጋፍ እንደሚያቀርብ ተጠቁሟል።
ለዘላቂ አየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ ለሚያቀርቡ 60 ወጣቶችም ሃሳባቸውን ወደ ዘላቂ የቢዝነስ ሞዴል እንዲያሳድጉ የሚያስችላቸው ሥልጠና እንደሚደረግላቸውም እንዲሁ።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ 45 ፈቃድ ያወጡ የአረንጓዴ ንግድ ባለቤቶችን ለማፍራትና ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ የሥራ እድል ለመፍጠር እቅድ መያዙም ተገልጿል።
የሪች ፎር ቼንጅ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ለምለም ስንቅነህ፤ ፕሮጀክቱ በአየር ንብረትና በአከባቢ ላይ ተፅጽዕኖ የማያሳድሩ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያሰፉ ያስችላል ብለዋል።
ፕሮጀክቱ አዳዲስ አረንጓዴ ፈጠራዎችን በማበረታታት ወጣቶች በዘላቂነት ኑሯቸውን ለማሻሻል እንዲችሉም ትልቅ እገዛ እንዳለውም ነው ያረጋገጡት።