በግንባታ ኢንዱስትሪው የሚታዩ ውስብሰብ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመፍታት እየሰራሁ ነው - ኮንስትራክሽን ባለስልጣን - ኢዜአ አማርኛ
በግንባታ ኢንዱስትሪው የሚታዩ ውስብሰብ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመፍታት እየሰራሁ ነው - ኮንስትራክሽን ባለስልጣን
አዳማ መጋቢት 06/2014 (ኢዜአ) የጥራት መጓደልና የብልሹ አሰራሮችን ጨምሮ በግንባታ ኢንዱስትሪው የሚታዩ ውስብሰብ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በተቀናጀ አግባብ ለመፍታት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በግንባታ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የንቅናቄ መድረክ ዛሬ በአዳማ አካሂዷል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ነገዎ በወቅቱ እንደገለጹት በግንባታ ኢንዱስትሪው ዘርፈ ብዙና ውስብስብ ችግሮች አሉ።
ባለስልጣኑ በዘርፉ ባካሄደው ጥናት ችግሮቹን በአራት ዋና ዋና ምድቦች መለየታቸውን ተናግረዋል።
ባላለቀ ዲዛይን ወደ ስራ መግባትና በየጊዜው ማሻሻያ ማድረግ፣ የዋጋ ሁኔታ ከወቅቱ ገበያና አቅርቦት ጋር ያለመሄድ፣ የፕሮጄክቶቹ ባለቤቶች ፍላጎቶች በየጊዜው መቀያየርና ክፍያ በወቅቱ ያለመፈፀም፣ ቅድመ ክፍያ ተቀብሎ በወቅቱ ያለመጀመር፣ የአቅም ውስንነትና የፕሮጄክት አመራር አቅም ማነስ በጥናቱ የተለዩ የዘርፉ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ችግሮቹን በተቀናጀ አግባብ ለመፍታት በሁሉም ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የጋራ ንቅናቄ ማስፈለጉን የገለጹት አቶ መስፍን "የመድረኩ ዓላማ ንቅናቄውን ለመፈፀምና ለማስፈፀም በጥናት ግኝቶች ላይ የጋራ ግንንዛቤ ይዘን ወደ ስራ ለመግባት ነው" ብለዋል።
ችግሮችን ለመቅረፍ አሰራርና ቴክኖሎጂን ከማሻሻል ጀምሮ ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሀገር ውስጥ ምርቶችን መጠቀምና ተጠያቂነት ያለበት የህግ ማዕቀፎችን ለመዘርጋት አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን በማከል።
የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሊድ አብዱረሃማን በበኩላቸው በግንባታ ኢንዱስትሪው የሚታዩ ውስብስብ ችግርችን ባለድርሻ አካላት አውቀው ለመፍትሄው የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የንቅናቄ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
"የህግ ማእቀፎችና አሰራሮቻች ላይ ሰፊ ክፍቶች አሉብን" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በየደረጃው ያሉ የዪኒቨርሰቲ አመራሮች፣ ተቆጣጣሪ ባለስልጣንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ለማስቻል መድረኩ ተዘጋጅቷል" ሲሉ አክለዋል።
ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከክልሎች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።