የሀዋሳ የታክሲ አሽከርካሪዎች ህገ-ወጥ የቤንዚን ንግድ መበራከት ለስራቸው ፈተና መሆኑን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የሀዋሳ የታክሲ አሽከርካሪዎች ህገ-ወጥ የቤንዚን ንግድ መበራከት ለስራቸው ፈተና መሆኑን ገለጹ

ሀዋሳ፣ መጋቢት 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) እየተበራከተ በመጣው ህገወጥ የቤንዚን ንግድ ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻሉና ለችግር መዳረጋቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀዋሳ ከተማ የታክሲ አሽከርካሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ቅሬታው ተገቢ መሆኑን አምኖ ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ተናግሯል።
ቅሬታ ካቀረቡት መካከል የባለሶስት እግር ባጃጅ አሽከርካሪ አቶ ደገፋ ሃይለማሪያም ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዕለት ሰርተው በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን ለሚያስተዳድሩበት የባጃጅ ታክሲ ቤንዚን ለመቅዳት ሁለት ቀን ተራ ጥበቃ ያለስራ ሰልፍ ይዘው ለማደር ተገደዋል።
"በከተማዋ በማደያዎች ላይ ቁጥጥር ባለመደረጉ በህገ ወጥ ንግድ የሚደረግ ቤንዚን ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ እየተበራከተ መምጣቱን ለእጥረቱ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል ።
በማደያዎች 32 ብር የሚሸጠው 1 ሊትር ቤንዚን በህገወጥ ገበያው እስከ 200 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ጠቁመው፤ ሁኔታው በስራቸው ላይ ጫና እያሳደረ በመሆኑ የሚመለከተው የመንግስት አካል ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቀዋል።
"በነዳጅ ማደያዎች ላይ የሚደረግ የቁጥጥር ስርዓት አነስተኛ በመሆኑና ህጋዊ ግብይት ባለመፈጸሙ ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረግን ነው" ያሉት ደግሞ የታክሲ አሽከርካሪ አቶ ዮሴፍ ኩማ ናቸው።
"ማደያዎችን የሚቆጣጠር አካል ባለመኖሩና በምሽት ዋጋ ጨምረው መሸጥ ስለሚፈልጉ ሰው ጸሀይና ብርድ እየተፈራረቀበት መብራት የለም በሚል ሰበብ ስራ ያቆማሉ፤ ከዚያም ተለምነው ሽያጩን ይጀምራሉ" ሲሉ ቅሬታውን ገልጸዋል።
የቤንዚን እጥረት ችግሩ የሚመነጨው በአቅርቦት ችግር ብቻ ሳይሆን በአስተዳደር ችግር ጭምር እንደሆነ ገልጸው፤ ህዝብን ለማማረር የሚፈጸመውን ሴራ የከተማው አስተዳደር መከላከል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በከተማው የታፍ ማደያ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ መስከረም ቱፋ ቤንዚን የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን እያስተናገዱ ቢሆንም ፍላጎቱ ከአቅርቦት በላይ በመሆኑ ችግሩ እንደተከሰተ ተናግረዋል።
የሞተር ሳይክሎችን ለመቆጣጠር የሚያስችል አሰራር ባለመኖሩ የቀዱትን ቤንዚን እየገለበጡ በጥቁር ገበያ እየሸጡ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የኢንስፔክሽንና ሬጉሌሽን ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መሰለ ከበደ "ከአሽከርካሪዎቹ የሚቀርበው ቅሬታ ተገቢ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
በሀዋሳ የቤንዚን እጥረት አለመከሰቱን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመፍታት አስተዳደሩ ግብረሃይል አቋቁሞ ጠንካራ የቁጥጥር ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
ባለፉት ሶስት ቀናት በተደረገ ቁጥጥር እየተመላለሱ የሚቀዱ 25 ተሽከርካሪዎችና በህገ ወጥ መንገድ ሽያጭ እንደሚያከናወኑ የተደረሰባቸው ሶስት ማደያዎች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ወደ ህግ የማቅረብና የማሸግ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።
በቁጥጥር ስራው በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስስ የነበረ ከ30 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን መያዙን አስታውቀዋል።
ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ተሽከርካሪዎችን በኩፖን የማስተናገድ ስርዓት እንደሚዘረጋ አመላክተዋል።
በሀዋሳ ከተማ በሚገኙ 16 የነዳጅ ማደያዎች በሳምንት የሚቀርበው ከ270 ሺህ ሊትር በላይ ቤንዚን በቂ በመሆኑ የሚስተዋለውን ሰው ሰራሽ እጥረት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼