አገልግሎቱ ከአፋር ክልል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ሚሊዩን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ ከአፋር ክልል ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ሚሊዩን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ
ሰመራ ሚያዝያ 04/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን ለክልሉ ያስረከቡት የአገልግሎቱ የኮሚዩኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወል ሃሰን እንደገለጹት የሽብር ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች በከፈተው ወረራ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት አስከትሏል።
የተጎጂዎችን ችግር ለማቃለል መንግስትና የተለያዩ ባለድርሻዎች እያደረጉ የሚገኘውን ጥረት ማገዝ የሁሉም ዜጋና ተቋማት ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል" ብለዋል።
የመድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት 470 ኩንታል የዳቦ ዱቄት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ድጋፉ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው መሆኑን ጠቁመው ተቋሙ በቀጣይም በማናቸውም መልኩ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከአፋር ህዝብ ጎን እንደሚቆም አስታውቀዋል።
የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ አደም አህመድ በበኩላቸው እንደተናገሩት በክልሉ በሽብር ቡድኑ ጥቃት ከ600 ሺህ በላይ አርብቶ አደሮች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
"ህዝቡ የእለት ደራሽ አርዳታ ጠባቂ እንዲሆን በመገደዱ በመንግስትና ሀገር ላይ ጫናው ከፍተኛ ነው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ያደረገው ድጋፍ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተጎጂዎችን ችግር የሚያቃልል መሆኑን ገልጸዋል።
አገልግሎቱ በአስቸጋሪ ወቅት ከህብረተሰቡ ጎን በመቆም ላደረገው ድጋፍ በተጎጂ ወገኖችና በጽህፈት ቤቱ ስም አመስግነዋል።