ኤጀንሲው በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ኤጀንሲው በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረገ
አርባምንጭ፤ መጋቢት 3/2014 (ኢዜአ)፡ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በቦረና ዞን በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ ድጋፍ አደረገ ፡፡
ድጋፉን በሞያሌ ከተማ በመገኘት ለተጎጂዎች ያስረከቡት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ ኤጀንሲው በቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ከ470 ኩንታል በላይ የስንዴ ዱቄት ድጋፍ ማመቻቸታቸውን ገልጸዋል፡፡
ድጋፉ በገንዘብ ሲተመን ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል ፡፡
ቀደም ሲልም በምግብ እጥረት ምክንያት በሚመጡ ተጓዳኝ በሽታዎች ህፃናትና እናቶች ለሞት እንዳይዳረጉ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ መድኃኒቶችን ማሰራጨታቸውን አስታውሰው፤ ''ህብረተሰቡ ከዚህ ችግር እስኪላቀቅ ድረስ ሁለንተናዊ ድጋፋችን ይቀጥላል'' ብለዋል ፡፡
''የቦረና ህዝብ በደጉ ጊዜ ውሀ ለጠየቀው ወተት በመስጠት የሚታወቅ ነው'' ያሉት ዶክተር አብዱልቃድር፤ ለአንድ ዓመት ያህል የተራዘመው የዝናብ እጥረት በአሁን ወቅት የከፋ ጉዳት እያስተናገደ መሆኑን ጠቁመዋል።
''ህብረተሰቡን ከችግር ለመታደግ ሁላችንም ያቅማችንን መደገፍ ይጠበቅብናል'' ብለዋል ፡፡
ኤጀንሲው ከዚህ ቀደም ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዲሁም በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
የቦረና ዞን አደጋ ሥጋት ሥራ አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ተጠሪ አቶ ጉዮ ጨርፊ በበኩላቸው፤ በአካባቢው ድርቅ አደጋ ከተከሰተ ስድስት ወራት ወዲህ ለተጎጂዎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል።
እስካሁን ለ600 ሺህ ወገኖች የሚሆን የ200 ሺህ ኩንታል የምግብ እህል አቅርቦት በመንግስት፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የህብረተሰብ ክፍሎችና ከተለያዩ ተቋማት ደግሞ ከ56 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል መቅረቡን ጠቅሰዋል ፡፡
ደርቁ በማህበረሰቡ ሥነ-ልቦናም ጭምር እያስከተለ ካለው መጠነ ሰፊ ጉዳት አንፃር እስካሁን የተደረገው ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለጋስና ሁሉን አቃፊ የሆነው ቦረና በአሁን ወቅት እያስተናገደ ያለውን ችግር በመረዳት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
በዞኑ የሞያሌ ወረዳ ነዋሪ አቶ አብዱብ ዋቆ፤ ከመንግስት ተቋማትና ከህብረተሰቡ እየተደረገላቸው ስላለው ሰብለዓዊ ድጋፍ አመሰግነው፤ድጋፉ ከችግራቸው አንፃር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
እስካሁን በድርቁ ምክንያት የሰው ሕይወት ባያልፍም ጉዳቱ በዚሁ ከቀጠለ ስጋት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ አብዱብ፤ ''የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ እንዲሁም ሌሎች አካላት ተረባርበው ሊረዱን ይገባል'' ብለዋል ፡፡
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችም በአካባቢው ያለውን ችግር በመገንዘብ የሚቻላቸውን እገዛ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል ፡፡
የሞያሌ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ዘይቱና አበራ በበኩላቸው፤ በድርቁ ውሃና የከብቶች መኖ በማጣት ከመቸገራቸውም ባለፈ በከተማ ያለው የኑሮ ውድነት ከባድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ የቦረናን ህዝብ ችግር ለማቃለል የሚችለውን ሁሉ እንዲያደርግ ጠይቀዋል ፡፡