ቀጥታ፡

በባህር ዳር ከተማ የዋጋ ንረትን በመከላከል ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ባህር ዳር ፤ መጋቢት 3/2014 (ኢዜአ) በባህር ዳር ከተማ በምግብ ዘይትና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት ለመከላከል ግብረ ኃይል በማዋቀር ገበያውን እያረጋጋ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የተዋቀረው የገበያ አረጋጊ  ጥምር ግብረ ኃይል እርምጃው ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ አካሂዷል።

በዚህ ወቅት የመምሪያው ኃላፊ አቶ አበበ አጥናፉ  እንደተናገሩት በከተማው ባልተጠበቀ ሁኔታ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመከላከል ጥምር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በተቀናጀ መንገድ እየሰራ ነው ።

ጥምር ግብረ ኃይሉ ለአንድ ሳምንት ባካሄደው ድንገተኛ ፍተሻም የችግሩ አባባሽ ሆነው በተገኙ 128 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን ገልጸዋል።

በዚህም ከ7 ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይትና ከ58 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ በሕገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ መገኘቱን አስረድተዋል።

ያለ አግባብ ተከማችቶ ከተገኘው ውስጥ ባለ አምስት ሊትር ዘይት ለህብረተሰቡ  በተመጣጣኝ እንዲሰራጭ መደረጉን ኃላፊው አስታውቀዋል።

ግብረ  ኃይሉ ህገ ወጥ እንቅስቃሴውን ከመከላከል በተጓዳኝ ከአለ በጅምላ ድርጅት 64 ሺህ ሊትር የፓልም ዘይት ተረክቦ ለነዋሪዎች ሊትሩን  በ77 ብር ሂሳብ እያከፋፈለ ነው ብለዋል።

ጥምር ግብረ ኃይሉ የዋጋ ንረቱን ለመከላከል የሚያደርገውን እንቅስቃሴውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባና የጥምር ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ባዬ አለባቸው፤  ያለአግባብ የተደገረው የዋጋ ጭማሬ ህብረተሰቡን ለከፋ ችግር እየዳረገው መሆኑን ተናግረዋል።

የግብረ ኃይሉ አባላት የከተማው ንግድ ስርዓት ለማስያዝና ህዝቡ ከተጋረጠበት  የኑሮ ጫና ለመታደግ  በቅንጅት መንቀሳቀስና ህገ-ወጦችን ተከታትሎ በመያዝ አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ያደርጋሉ ብለዋል።

አስተዳደሩ ዘይትና ሌሎች የግብርና ምርቶችን እጥረት ችግር ለማቃለል ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበራት 10 ሚሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ብድር መመቻቸቱን ገልጸዋል።

በዘይትና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ እየታየ ያለውን የተጋነነ የዋጋ ንረት የምንከላከለው ተቀናጅተንና ተናበን መስራት ስንችል ነው ያሉት ደግሞ የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ጌታቸው ስንሻው ናቸው።

በየደረጃው ያለው አመራር ድጋፉን  አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በውይይት መድረኩ ከከንቲባ ጽህፈት ቤት፣  ከፖሊስ፣ ከደንብ ማስከበር፣ ከማህበራት፣ ከገቢዎች፣ ከትራንስፖርት፣ ከግብርናና ሌሎች ተቋማት የተውጣጡ የጥምር ግብረ ኃይል አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም