ቀይ መስቀል በድርቅና ግጭት ተጋላጭ የሆኑ አካላትን በጥናት በመለየት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ቀይ መስቀል በድርቅና ግጭት ተጋላጭ የሆኑ አካላትን በጥናት በመለየት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል
ጎባ፤ መጋቢት 3 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ድርቅና ጦርነት ያስከተለውን ጉዳት በጥናት በመለየት ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ አካላት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የማህበሩ የቦርድና ከፍተኛ አመራሮች በባሌ ዞን ጎሮ ወረዳ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ ጌታቸው ታአ በወቅቱ እንዳሉት፤ ማህበሩ በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ድርቅና ጦርነት ያስከተለውን ጉዳት በጥናት በመለየት ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ አካላትን በመርዳት ላይ ይገኛል፡፡
ማህበሩ በሁለቱ የባሌ ዞኖች ለሚገኙ ሶስት ወረዳዎች ውስጥ ለድርቁ ተጋላጭ ለሆኑ ከ1ሺህ150 ለሚበልጡ አባወራዎች በአንደኛው ዙር 340 ኩንታል ዱቄትና 2ሺህ ሊትር ዘይት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።
ድጋፉም ከ5ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ እንዳለው ነው የገለጹት።
በሁለተኛው ዙር ደግሞ በዞኑ ለጎሮ ወረዳ ድርቅ ተጎጂዎች ከዓይነት ድጋፍ ይልቅ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው ይህም ተጎጂዎቹ በራሳቸው የሚፈልጉትን ገዝተው ለመጠቀም የሚያስችላቸው ነው ብለዋል።
አቶ ጌታቸው እንዳስረዱት፤ ለ500 አባወራዎች ለእያንዳንዳቸው 4ሺህ ብር ለማስተላለፍ የሚያስችል የተጠቃሚዎች የባንክ ሂሳብ ቁጥር እየተከፈተላቸው ይገኛል፡፡
እስካሁን 300 የሚሆኑ ሰዎች የባንክ ሂሳብ የከተከፈተላቸው ሲሆን በዚህ ሳምንት ለተቀሩት በመክፈትም ገንዘቡ የሚተላለፍላቸው ይሆናል ብለዋል፡፡
ድጋፉ በገንዘብ መሆኑና በቀጥታ በተጎጂዎቹ የባንክ ሂሳብ ላይ ገቢ መደረጉ ብልሹ አሰራሮችን ለማስቀረትና የህብረተሰቡንም የቁጠባ ባህል ለማሳደግ ሁነኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡
በማህበሩ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድጀማል አባቦራ፤ ማህበሩ በክልሉ ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን በጥናት በመለየት የእለት ድጋፍና በቋሚነት እንዲቋቋሙም ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በባሌ ዞን ጎሮ ወረዳ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው ዘመናዊ የመስኖ ልማት ፕሮጄክት የእዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ከተጎጂዎቹ መካከል ወይዘሮ ፋጡማ ባቲ በሰጡት አስተያየት፤ በማህበሩ የባንክ ሂሳብ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እየተከፈተላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ ከድርቁ አገግመው የተረጋጋ ኑሮ ለመምራት እንዲችሉ መንግስት የምርጥ ዘርና ሌሎች ዘላቂ ድጋፎችን እንዲደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡
በችግር ጊዜ ሁሉ ከጎናችን ለሚሆነው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ምስጋናችን የላቃ ነው ያሉት ደግሞ የወረዳው የሀገር ሽማግሌ አቶ መሐመድ ሶሞ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በአሁኑ ወቅት ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን አባላት እንዳሉት ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡