ቀጥታ፡

ሰላምና መረጋጋት በማስፈን የህብረተሰቡን ኑሮ ማሻሻል ቅድሚያ የሚሰጠው የትኩረት መስክ ነው - ብልጽግና ፓርቲ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት በማስፈን የህብረተሰቡን ኑሮ ማሻሻል ቅድሚያ ሰጥተው የሚሰሩበት የትኩረት መስክ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ገለጹ፡፡

በወላይታ ዞን የብልጽግና ፓርቲ አመራር የሆኑት አቶ ሳሙኤል ፎላ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት ዓመታት ዜጎች በማያውቁት ጉዳይ በግፍ ተገድለዋል፤ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።

በመሆኑም የዜጎች በማንነታቸው ወይም በሌላ መንገድ መገደል፣ መፈናቀልና እንግልት ቀርቶ ባሉበት ቦታ ሁሉ ሰርቶ ሃብት የማፍራትና በሰላም የመኖር ህገ መንግስታዊ መብታቸው እንዲከበር እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ገብረፃድቅ ገብረመድህን፤ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት አስጠብቆ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎችም ተጠቃሚ ማድረግ ከእኛ ይጠበቃል ብለዋል።

የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ አመራር አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ በላይ ጉዳይ የለንም ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ በጉባኤው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች እንዳሉ ሆኖ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተፈፃሚ እንዲሆኑ የአመራሩን ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

በመሆኑም በተሰማራንበት የመንግስት መዋቅር በፓርቲው የተላለፉ ውሳኔዎች እውን ሆነው የዜጎች ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ የማድረግ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡም በህልውና ዘመቻው ከመንግስት ጎን ሆኖ እንደተፋለመው ሁሉ በህግ ማስከበር ዘመቻውም ሊያግዝ ይገባል፤ ይህ ሲሆን አገር ሰላም ትሆናለች ብለዋል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ፤ የኢትዮጵያ ትልቁ ተግዳሮች የኑሮ ውድነትና ስራ አጥነት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሰላምና ደህንነት እንዲሁም በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤው የሚያሳልፋቸው ውሳኔዎች በመንግስት መዋቅር ተፈጻሚ እንዲሆኑ ተግተው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም