ለአገራዊ ምክክር መድረኩ ስኬት የሲሺል ማኅበራት የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ለአገራዊ ምክክር መድረኩ ስኬት የሲሺል ማኅበራት የበኩላቸውን ሚና መወጣት ይጠበቅባቸዋል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለአገራዊ ምክክር መድረኩ ስኬት የሲሺል ማኅበራት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ባለሥልጣን ገለፀ።
ባለሥልጣኑ ይህን ያለው "የኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት" የተሰኘ የሲቪል ማኅበር ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመተዋወቅ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ የዜጎች መብት ማስተባባሪያ ድርጅት ከ10 ዓመት በፊት በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ የተመሰረተ ሲሆን በኢትዮጵያ ደግሞ በ2013 ዓ.ም በሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች ኤጀንሲ ተመዝግቦ እየተንቀሳቀሰ ያለ ድርጅት ነው።
በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ፤ እንደ ሀገር የታሰቡ አሻጋሪ ሃሳቦች ለማሳካት የሲቪል ማኅበራት ሚና አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የሲቪል ማኅበራት ኢትዮጵያ በጀመረችው የለውጥ እንቅስቃሴ በልማት፣ በዴሞክራሲና በሰላም ግንባታ የበኩላቸውን አስተዋፆ እያበረከቱ እንደሚገኙ አንስተዋል።
ለአብነትም በ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመታዘብ እንዲሁም መራጮች ስለ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በማድረግ ሰላማዊ፣ ታዕማኝነት ያለው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እውን እንዲሆን አስተዋፆ ማበርከቱን ተናግረዋል።
የሲሺል ማኅበራት በቀጣይ የሚደረገው አካታች አገራዊ የምክክር መድረክ ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ጂማ ዲልቦ አሳስበዋል።
በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በማድረግና በማይናወጥ መሰረት ላይ ለማጽናት የሚተጉ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ያስፈልጋሉ ብለዋል።
አካታች የሆነ ማንም የማይገለልበት፣ የሁሉም ዜጋ መብት እኩል የሚከበርበት አገር ለመፍጠርና በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ ዜጋ ለመፍጠር የሲቪል ማኅበራት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
የኢትዮጵያዊነት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሰላም አለሙ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊነት ለሁሉም የሚጠቅምና በሁሉም ዘንድ ተቀባይነትና ተዓማኒነት እንዲኖረው የማድረግና የማስፈፀም ሃላፊነት ለመንግሥት ብቻ የተጣለ አይደለም ብለዋል።
ሃላፊነቱ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ በመሆኑ በዚህ ረገድ ድርጅቱ ሃላፊነቱን ለመዋጣት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራት ባህል ማስቀጠል እንዲቻል በመመካከርና በመነጋገር ላይ መመስረት እንደሚገባው ገልፀው ለዚህ ደግሞ የሁሉንም ጥረትና ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ነው የተናገሩት።