ቀጥታ፡

የትግራይ ኃይሎች በአማራና አፋር ክልሎች 346 ንጹሃን ዜጎች ሕገወጥና ከዳኝነት ውጪ የሆነ ግድያ ፈጽመዋል - ኢሰመኮ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የትግራይ ኃይሎች በአማራና አፋር ክልሎች 346 ንጹሃን ዜጎችን ሕገወጥና ከዳኝነት ውጪ ግድያ መፈጸሙን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ።

የትግራይ ኃይሎች “ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን በሚችል መልኩ”የእገታ እና አስገድዶ መሰወር ተግባራትን ፈጽመዋል” ብሏል።

ኮሚሽኑ በአፋር እና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ የምርመራ ሪፖርት ትናንት ይፋ አድርጓል።

በሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም የትግራይ ኃይሎች በአፋርና አማራ ክልሎች በከፈቱት ወታደራዊ ጥቃት በርካታ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎም ሰፊ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መከሰታቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

ኢሰመኮ ከመስከረም እስከ ታህሣስ ወር 2014 ዓ.ም ድረስ ባሰማራው የሰብአዊ መብቶች ምርመራ ቡድንና ተከታታይ የምርመራ ስልቶች በአፋርና አማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በቆየው ጦርነት የተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን ምርምራ ማድረጉንና በግኝቱም በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን አመልክቷል።

ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች “በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች በተለይም እና በዋነኝነት በትግራይ ኃይሎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች በሕገወጥ መንገድ መገደላቸውን” ማረጋገጡን ገልጿል።

ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው አካባቢዎች ሆነ ተብለው የተፈጸሙ ሕገወጥ ግድያዎችን ሳይጨምር፣ በጦርነት ውስጥ በሲቪል ሰዎች ላይ በደረሰ የሕይወትና የአካል ጉዳት ብቻ ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች ለሞት፤ እንዲሁም 309 ሲቪል ሰዎች ለቀላል እና ለከባድ የአካል ጉዳት መዳረጋቸውን አመልክቷል።

የትግራይ ኃይሎች በአማራና አፋር ክልሎች የሚገኙ ከተሞችን ከመቆጣጠራቸው አስቀድሞ ከተሞች ላይ በተኮሷቸው ከባድ መሳሪያዎች ሲቪል ሰዎች እንዲሞቱ እና እንዲቆስሉ አድርገዋል ብሏል።

ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ በአፋር ክልል በፈጸሙት ጥቃት 27 ሕፃናትን ጨምሮ 107 ሲቪል ሰዎችን መግደላቸውንና 35 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን አመልክቷል።

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ዳባት ወረዳ ጭና ቀበሌ ከነሐሴ 24 እስከ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በቀበሌው በቆዩበት ወቅት ቢያንስ 47 ሲቪል ሰዎችን (41 ወንዶች እና 6 ሴቶች) እንደተገደሉም ተገልጿል።

የትግራይ ኃይሎች አካባቢዎችን በሚቆጣጣሩበት ወቅት “በትግራይ ኃይሎች ላይ ለደረሰባቸው ጥቃት ወይም የትግራይ ታጣቂዎች እና ትግራይ ላይ ለደረሰ ሞት እና ጉዳት የበቀል/አጸፋ እርምጃ መሆኑን ጭምር በግልጽ እየተናገሩ ብዙ ሲቪል ሰዎችን በጅምላ እና በነጠላ ገድለዋል” ሲል ሪፖርቱ ይጠቅሳል።

የትግራይ ታጣቂዎች በአማራ ክልል ጭና ቀበሌ አንድን አባት ከገደሉ በኋላ የ7 ዓመት ሕፃን ልጃቸውንም “ይህ አድጎ ነው የሚወጋን” ብለው በእናቱ ፊት በጥይት ተኩሰው መግደላቸውን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

ታጣቂዎቹ ከፈጸሙት ግድያና ካደረሱት የአካል ጉዳት በተጨማሪ በሲቪል ሰዎች ላይ በጭካኔ የመደብደብ፣ የማዋረድ እና የማሰቃየት ተግባር መፈጸማቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል።

የትግራይ ኃይሎች በአፋርና አማራ ክልሎች የሚገኙ ቦታዎችን ተቆጣጥረው በቆዩበት ጊዜ መጠነ ሰፊ፣ ጭካኔ የተሞላበትና ስልታዊ የሆነ በተናጠል እና በቡድን የተፈጸመ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በሴቶች፣ በሕፃናት ሴቶችና አረጋዊያን ሴቶች ላይ ማድረሳቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።

 “የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በሴቶች ላይ የፈጸሙት ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃትን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለጦርነት ዓላማ እንዳዋሉት የሚያስረዳ ነው” እንደሆነ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የትግራይ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን በሚችል መልኩ የእገታ እና አስገድዶ መሰወር ተግባራትን መፈጸማቸውን ገልጿል።

የፌዴራል፣ የአማራ እና የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዐውድ ውስጥም ቢሆን የጥብቅ አስፈላጊነት፣ የተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነጻ የመሆን መርሆዎች ከሚፈቅዱት ውጪ መጠነ ሰፊ የዘፈቀደ እስር መፈጸማችውን ኮሚሽኑ አመልክቷል።

በተመሳሳይ የ”ኦነግ ሸኔ” ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች በነበሩ የመንግሥት አስተዳደር ኃላፊዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ ያሏቸው ሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያን መፈጸማቸውን በሪፖርቱ የተገለጸው።

በሰዎች ላይ ከተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶ በተጨማሪ የግለሰቦች ንብረት፣ አገልግሎት ሰጪ የመንግስት እና የግል ተቋማት በትግራይ ሃይሎች መዘረፋቸውና መውደማቸው ተገልጿል።

ሪፖርት ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች የተፈጸሙ ሁሉንም ጥሰቶችን የሚሸፍን አለመሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ ሆኖም ምርመራው በተከናወነባቸው ስፍራዎች የተፈጸሙ ዋና ዋና የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ዋነኛ ጠባዮችና ሁኔታዎችን እና አጠቃላይ የጥሰት ዓይነቶችን ወካይ በሆነ መልኩ ማካተቱን አመለክቷል።

በሪፖርቱ የተካተቱን ምክረ ሃሳቦች የመተግበሩ ሂደት በአፋጣኝ እንዲጀመር ኮሚሽኑ ለሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጥሪ አቅርቧል።

ኮሚሽኑ በአማራና አፋር ክልሎች በሚገኙ ስምንት ዞኖች 427 ሚስጢራዊ ቃለመጠይቆችን፣136 ከተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት አመራሮችና 12 የቡድን ውይይቶችን በማድረግ ሪፖርቱን ማዘጋጀቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ ጋር በመሆን በትግራይ ክልል ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ ስለነበረው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም የጣምራ ምርመራ ሪፖርት ማውጣታቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም