ሁሉም ስለ ሰላም፣ ይቅርታ እና አንድነት ሊጸልይ ይገባል - ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉም ስለ ሰላም፣ ይቅርታ እና አንድነት ሊጸልይ ይገባል - ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሁሉም ስለ ሰላም፣ ይቅርታ እና አንድነት ሊጸልይ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አስገነዘቡ።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ቀዳማዊ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የስንብት መርሃ ግብር ላይ ባስተላለፉት የሀዘን መልዕክት ለህዝብ እና ለአገር በጎ የዋሉትን መሸኘት የተለመደ እና ባህላችን ነው ብለዋል።
ብጹዕ አቡነ መርቆሬዎስ ለአገራቸው በርካታ መልካም ነገሮችን ማበርከታቸውን ገልፀው፤ ለቤተክርስቲያኗም ሰፊ መንፈሳዊ አገልግሎት ማበርከታቸውንም ገልጸዋል።
“አባታችን በአጸደ ስጋ ቢያርፉም በነፍሳቸው ህያው ሆነዋል ይኖራሉ” ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በምድር እያሉም መልካም ተግባራትን አከናውነው የገጠማቸውን መከራም በትዕግሥት ያለፉ ታላቅ አባት እንደነበሩም አንስተዋል።
“ብጹዕ አቡነ መርቆሬዎስም ከመከራው ዓለም ወደ ዘላለማዊ ህይወት ተሸጋግረዋል” በማለት ገልጸው፤ እግዚአብሔር ሰላሙን እንዲሰጠን ፍቅሩን እንዲያድለን ችግሩን እንዲያስወግድልን መስራት አለብን ሲሉ መክረዋል።
ሁሉም የእምነት አባቶች መከራው እንዲወገድ እግዚአብሔር በሚወደው መንገድ እንድንጓዝ መጸለይ ማስተማር ይገባልም ብለዋል።
በስንብት መርሃ ግብሩ ላይ የተለያዩ የእምነት ተቋማት መሪዎችም ተገኝተው የሀዘን መልዕክት በማስተላለፋቸውም ምስጋና አቅርበዋል።
የስዊዲን አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ኤሊያስ ባስተላለፉት መልዕክት ዕለቷ ለኢትዮጵያ የተመረቀች ቀን ናት ብለዋል።
ዕርቁ ከተፈጸመ በኋላ አሁን አንገባም የሚል ሃሳብ አቅርቤ ነበር ያሉት አቡነ ኤሊያስ ነገር ግን በፈጣሪ ፍላጎት ሁሉም ሆኗል ብለዋል።
እግዚአብሔርን ለኢትዮጵያ ምህረትን እና አንድነትን እንዲሰጥም የመልካም መልዕክት ምኞታቸውንም አስተላልፈዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼