በአንድነትና መከባበር ግድያና ማፈናቀልን ማስቆም ይገባል - ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመለያየትን ኃሳብ በመተው በአንድነትና መከባበር ግድያና ማፈናቀልን ማስቆም እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የአስክሬን ሽኝት መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች  ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ እረፍት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።

ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጂ ዑመር ኢድሪስ የሰውን ልጅ የሚያከብረውና የሚያስከብረው ስራው፣ ጥረቱና እዘነቱ ነው ብለዋል።

ብጹዑነታቸው ለዓመታት ከስደት ሲኖሩበት ከነበረው ሀገረ አሜሪካ ሲመጡ ለኦርቶዶክስ አንድነት መልካም ምኞት ማስተላለፋቸው አስታውሰዋል።

የሰውን ልጅ መልካም ስራና ምግባር እንደሚያስከብረው ከእርሳቸው መማር እንደሚገባም ገልጸዋል።

ከመንግስት ጀምሮ የኃይማኖት አባቶቹ ክርስቲያን ሙስሊሙ፣ በመዋደድ በመከባበር ግድያና መፈናቀልን እንዲያስቆም ጥሪ አቅርበዋል።

መልካም ተግባርን ብቻ ማከናወን እንደሚገባም የአደራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሽኝት መርኃግብሩ የሀገር ውስጥና ከዓለም አቀፍ  ኃይማኖት ተቋማት የተወከሉ የየእምነቱ መሪዎች መሪዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም