ቀጥታ፡

ብፁዑ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የይቅርታ፣ የትህትና እና የፍቅር ምሳሌ ናቸው - ቄስ ዮናስ ይገዙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዑ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የይቅርታ፣ የትህትና እና የፍቅር ምሳሌ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነየሱስ ፕሬዚዳንት ቄስ ዮናስ ይገዙ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የአስክሬን ሽኝት መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ቄስ ዮናስ ይገዙ በብጹዕነታቸው እረፍት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።

የምንወዳትና የምናከብራት ቤተክርስቲያን ለምዕመኖቿና ሌሎች እምነት ተከታዮችም ምሳሌ የሚሆኑ አባቶችን አፍርታለች።

ቤተክርስቲያኗ በኢትዮጵያ ላሉ እምነቶች ሁሉ እናት ነች ብለዋል።

በስፍራው የመገኘታቸው ምስጥርም ልጅ ወላጁን መሸኘት ስላለበት እንደሆነ አንስተዋል።

መካነየሱስ ቤተክርስቲያንም ከቤተክርስቲያኗ ጋር የሚጋሩት ሰፊ አስተምህሮ እንዳለ ገልጸዋል።

ሀዘኑ መሪር ቢሆንም ብፁዕነታቸው ግን የይቅርታ፣ የትህትና እና የፍቅር ምሳሌ ናቸው።

ከብጹዕነታቸውም ፍቅርን፣ ይቅርታንና ተስፋን መማር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የብጹዕነታቸውን ፈለግ መከተል እንደሚገባ አንስተው ለመላ የእምነቱ ተከታዮችም መጽናናትን ተመኝተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም