ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በፍቅር፣ ሰላምና ትብብር እንድንኖር ትምህርት ሰጥተውን ያለፉ አባት ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በፍቅር፣ ሰላምና ትብብር እንድንኖር ትምህርት ሰጥተውን ያለፉ አባት ናቸው
መጋቢት 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በፍቅር፣ ሰላምና ትብብር እንድንኖር ትምህርት ሰጥተውን ያለፉ አባት ናቸው" ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በመስቀል አደባባይ እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የአስክሬን ሽኝት መርሃ-ግብር ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመርሃ ግብሩ ላይ የስንብት አበባ ጉንጉን ያስቀመጡ ሲሆን፤ በብጹዕነታቸው እረፍት የተሰማቸውን ሃዘን በክብር መዝገብ ላይ አስፍረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ለ26 ዓመታት ተለያይቶ የነበረውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አንድ እንዲሆን ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ብጹዕነታቸው በስደት ከቆዩበት አሜሪካ ወደ አገራቸው እንዲመጡ በነበረን ውይይት መጠነኛ ክርክር ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብጹዕነታቸው ግን "የመዳን ቀን ዛሬ ነው፤ እኔ ከልጄ ጋር እሄዳለሁ" ብለው መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ አገራቸውንና ህዝባቸውን ያገለገሉ አባት ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡
"በእንባ፣ በጸሎት ያግዙኝ ነበር፤ አልፎ አልፎ ፈታኝ የሆነ ነገር ሲገጥመን ቢሮ ድረስ በመምጣት በጽሑፍ ምክርና ጸሎት ያደርጉልኝ ነበር" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
እርሳቸውን ማጣት ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ሀዘን ነው ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ታይቶና ተሰምቶ የማይጠገብ ዜማ፣ ታሪክና እሴት ባለቤት ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፍቅርና አንድነት ይህን እሴት ለዓለም ማስተዋወቅ አለብን ብለዋል፡፡
የኦርቶዶክስ ኃይማኖትን ከቀኖናዋ፣ ከታሪኳ እና ከትውፊቷ ጋር ለትውልድ ለማስተላለፍ ሁላችንም በትብብር መስራት አለብን ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በፍቅር፣ ሰላምና ትብብር እንድንኖር ትምህርት ሰጥተውን አልፈዋል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ሀገርን በዘላቂነት እናልማ
የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ
ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ