ቀጥታ፡

የቱርክ የፓርላማ አባላት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የቱርክ የፓርላማ አባላት ተወካዮች ከኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ተወያዩ።

በብልጽግና ፓርቲ የመጀመሪያ ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የገቡት የቱርክ ጀስቲስ እና ዴቬሎፕመንት ፓርቲ ተወካዮች እንዲሁም የቱርክ የፓርላማ አባላት ተወካዮች ከጉባኤው ጎን ለጎን ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ እንዲሁም በሰብዓዊ ድጋፍ ቱርክ ከኢትዮጵያ ጎን እንደምትቆም የቱርክ የፓርላማ አባላት በውይይቱ ወቅት ገልጸዋል፡፡  

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ፋቲ ማሃዲ ከቱርክ የምክር ቤት አባላት ተወካዮች ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲሁም በልማቱ ዘርፍ የቱርክ ድጋፍ እንደማይለይ መናገራቸውን ዶክተር ፋቲ ገልጸዋል።

የቱርክ-ኢትዮጵያ ፓርላማ ወዳጅነት ቡድን ሊቀ-መንበር መሃመት ሴይንት፤ ቱርክ ለኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዘርፍ በርካታ ድጋፎችን ማድረጓን ገልጸዋል፡፡፡

በቀጣይም በባህል ልውውጥ፣ በትምህርት እና በሌሎችም ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በቅንጅት እንሰራለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ወሳኝ ሚና እንዳለው ቱርክ ታምናለች ያሉት ሊቀ-መንበሩ ለዚህም ስኬት ቱርክ ከኢትዮጵያ ጎን ነች ብለዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ የሚያካሂደው የመጀመሪያው ጉባኤም በኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ አስተዋጽኦ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እና ቱርክ የሁለትዮሸ ግንኙነት 126 ዓመታትን ማስቆጠሩን መረጃዎች ይጠቁማሉ።     

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም