ከፈተና ወደ ልዕልና ያልንበት ዋና ምስጢር በማንኛውም ሰአት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ወደ ድል መቀየር የምንችል መሆኑን ለማሳየት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ከፈተና ወደ ልዕልና ያልንበት ዋና ምስጢር በማንኛውም ሰአት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ወደ ድል መቀየር የምንችል መሆኑን ለማሳየት ነው

መጋቢት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ከፈተና ወደ ልዕልና ያልንበት ዋና ምስጢር በማንኛውም ሰአት የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች ወደ ድል መቀየር የምንችል መሆኑን ለማሳየት ነው” ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ መክፈቻ ላይ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስት ዐቢይ አህመድ እንዳሉት፤ ብልፅግና በኢትዮጵያ ታሪክ ከነበሩ ፓርቲዎችና ድርጅቶች በቁጥርም በአደረጃጀትም ይለያል።
ብልጽግና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ግዙፍ ፓርቲ ነው ያሉት የፓርቲው ፕሬዚዳንት፤ በህዝብ ግፊት በለውጥ ፈላጊ አመራሮችና በፈጣሪ እርዳታ ብልጽግና መወለዱን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ብልጽግና ልዩ የሚያደርገው በመጤ ሳይሆን በሀገር በቀል እሳቤ የተመሰረተ ፓርቲ መሆኑ ነው ብለዋል።
ብልጽግናን በአንደኛ ጉባኤያችን ላይ ሆነን የምናየው ሁሉም ብሄሮች የተወከሉበት መሆኑን ነው ሲሉ ገልጸው፤ ፓርቲው ከሁሉም አካባቢ ከሁሉም ብሄር የተወከሉበት ኢትዮጵያን መስሎ ኢትዮጵያን ሆኖ የመጣ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።
ፓርቲያችን ገና ብዙ መስራት ቢጠበቅብንም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ እና ሰላማዊ ምርጫ ማረጋገጥ የቻለ ፓርቲ ነው በማለት ተናግረው፤ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላትን የካቢኔ አባል በማድረግ አካታችነቱን ማሳየቱን አውስተዋል።
የጉባኤው መሪ ሃሳብ ከፈተና ወደ ልዕልና የተባለበት ዋና ምስጢር በማንኛውም ሰአት የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ወደ ዕድል መቀየር የሚችል ፓርቲ መሆኑን ለማሳየት እንደሆነም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼