ብልጽግና በ"መደመር" እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጣናዊ ትብብርና አንድነት እንዲጠናከር የላቀ ሚና እየተወጣ ያለ ፓርቲ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ብልጽግና በ"መደመር" እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጣናዊ ትብብርና አንድነት እንዲጠናከር የላቀ ሚና እየተወጣ ያለ ፓርቲ ነው
መጋቢት 2/2014/ኢዜአ/ ብልጽግና በ"መደመር" እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጣናዊ ትብብርና አንድነት እንዲጠናከር የላቀ ሚና እየተወጣ ያለ ፓርቲ መሆኑን የጅቡቲው ገዥ ፓርቲ "ፒፕልስ ራሊ ፎር ፕሮግረስ" ገለጸ።
የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ ላይ በተጋባዥነት የውጭ የአገራት እህት ፓርቲዎች እንዲሁም የአገር ውስጥ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ የጅቡቲ "ፒፕልስ ራሊ ፎር ፕሮግረስ" ፓርቲ ዋና ፀሐፊና የሀገሪቱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር ኢልያስ ሙሳ ዳዋሌህ መልእክት አስተላልፈዋል።
የኢትጵያና ጅቡቲ ወዳጅነት ዘመን ተሻጋሪ መሆኑን ገልጸው፤ የፓርቲ ለፓርቲ ትብብሩም ይበልጥ እየጎለበተ ይሄዳል ብለዋል።
በንግግራቸውም ብልጽግና ፓርቲ ተራማጅ የፖለቲካ አስተሳሰብ ሰንቆ የኢትዮጵያን ሰላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ እየጣረ ያለ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ አካታች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ለመገንባት በተግባር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን እንገነዘባለን ብለዋል።
ብልጽግና በመደመር እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ ቀጣናዊ ትብብርና አንድነት እንዲጠናከር የላቀ ሚና እየተወጣ ያለ ፓርቲ መሆኑንም ተናግረዋል።
አገራዊ ምክክሩ ተሳክቶ ኢትዮጵያን እየፈተናት ያለው ችግር እንዲወገድና ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና እውን እንዲሆን ፓርቲያቸው ከብልጽግና ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል።
ፓርቲው ከተመሰረተ ጀምሮ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር ያደረገው ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ በመደመር እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፈው በቀጣናው አገራት ወደ አንድነትና ትብብር ለማምጣት እንደሰሩ አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያና ጅቡቲ ህዝቦች በደም የተሳሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ህዝባዊ ትስስሩን ወደ ላቀ ከፍታ ለማድረስ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትን እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።
የጅቡቲ ህዝብ እና መንግስት አንድነቷ የተጠበቀ፣ ጠንካራ የበለጸገች ኢትዮጵያ እንድትኖር ይሻል ያሉት ተወካዩ፤ የኢትዮጵያ መጠናከር ከራሷ አልፎ ለጅቡቲ፣ ለቀጣናውና ለአፍሪካ ደጀን ይሆናል ብለዋል።
"ኢትዮጵያ የግድ ማሸነፍ አለባት፤ ኢትዮጵያ አንድ መሆን አለባት፤ ችግሮቿን ካለውጭ ጣልቃገብነት ነፃ ሆና በራሷ መፍታት ትችላለች" ብለዋል።
'ድር ቢያብር አንበሳ ያስር' በሚለው የኢትዮጵያዊያን መርህ ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን እንደሚያጠናክሩም አረጋግጠዋል።
የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንትና የኤስ ፒ ኤል ኤም ምክትል ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር ጀምስ ዋኒ ኢጋ በበኩላቸው፤ በፓርቲው ቀዳማዊ ጉባኤ በመገኘታቸው ደስታቸውን ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፤ ፓርቲው በአካታችነት የህዝብን አንድነት መርህ ያደረገ ፓርቲ እንደሆነም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ መዲና እና የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ጠቅሰው፤ ፓርቲያቸው ኤስ ፒ ኤል ኤም ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመመስረት ቁርጠኛ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ ከአጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮ ለደቡብ ሱዳን ነጻነት ትግል ውለታዋ ከፍተኛ እንደነበር፤ የምድራችን ትልቁ ውለታም ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ከከፈለችው ውለታ በላይ አይሆንም ነው ያሉት።
የሁለቱ አገራት አጋርነት ዛሬም ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተው፤ ወዳጅነታቸውን በኢኮኖሚ መስክ፣ በጋራ ልማት እንዲያጎለብቱና በመንገድ መሰረተ ልማት እንዲተሳሰሩ ለማድረግ በጋራ እንሰራለን ነው ያሉት።