የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሽኝት መርሐግብር ነገ ጠዋት ከሃሌሉያ ሆስፒታል በመነሳት በመስቀል አደባባይ ይከናወናል - ኢዜአ አማርኛ
የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሽኝት መርሐግብር ነገ ጠዋት ከሃሌሉያ ሆስፒታል በመነሳት በመስቀል አደባባይ ይከናወናል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 02 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አራተኛው ፓትርያርክ የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሽኝት መርሐግብር ከነገ ጠዋት ሁለት ሰዓት ጀምሮ ከሀሌሉያ ሆስፒታል በመነሳት በመስቀል አደባባይ እንደሚከናወን ቅዱስ ሲኖዶስ አስታወቀ።
የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን የሽኝት መርሐግብርና ስርዓተ ቀብርን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ "ቅዱስነታቸው ካረፉበት ዕለት አንስቶ ዐቢይ ኮሚቴ በማቋቋም የተለያዩ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል" ብለዋል።
በዚህም መሰረት ከሐሙስ መጋቢት 01 ቀን እስከ አርብ መጋቢት 02 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ይፋዊ የሐዘን ቀን ታውጆ የእምነት ተቋማት መሪዎች፣ የመንግስት ባለስልጣናት ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሪዎችና ተከታዮች፣ የሀገራት አምባሳደሮች እና ምዕመናን በመንበረ ፓትርያርክ ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ በመገኘት በሀዘን መግለጫ መዝገብ ላይ ሐዘናቸውን እየገለጹ ይገኛል ሲሉ አስታውቀዋል።
“በነገው እለት ቅዳሜ መጋቢት 03 ቀን ደግሞ የቅዱስነታቸው አስከሬን ከሃሌሉያ ሆስፒታል በክብር ወደ መስቀል አደባባይ ያመራል” ያሉት አቡነ ዮሴፍ፤ በመስቀል አደባባይ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ምዕመናንና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት የእለቱ መርሐግብር ተከናውኖ አስከሬናቸው በክብር ታጅቦ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ጉዞ ማድረግ ይጀምራል ብለዋል።
በመንበረ ፓትርያርክ ጸሎተ ወንጌል ደርሶ ልዩ የሐዘን መግለጫና መንፈሳዊ መልዕክቶች ከተላለፉ በኋላ ወደ መንበረጸባኦት ቅድስትሥላሴ ካቴድራል የክብር ሽኝት እንደሚደረግም ገልጸዋል።
በካቴድራሉ ሌሊቱን የተለያዩ ስርዓቶች ከተከናወኑ በኋላ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ብጹዓን አባቶች፣ የአኃት አብያተ ክርስትያናት ተወካዮች፣ የመንግስት ባለስልጣናትና ምዕመናን በተገኙበት ስርዓተ ቀብራቸው ይፈጸማል ብለዋል።
ቅድስት ቤተክርስትያን በቅዱስነታቸው ሞት ያለችበትን ሐዘን በመመልከት ምዕመናን የቅዱስነታቸውን ሽኝት ከፍ ባለ ክብርና በፍጹም ኦርቶዶክሳዊ ጨዋነት እንዲያከናውኑ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ያሉት አቡነ ዮሴፍ ቀኖና ቤተክርስትያንን መሠረት ያላደረጉና ማንኛውም አግባብ ያልሆነ እንቅስቃሴ እንዳይኖር አጥብቀን እናሳስባለን ብለዋል።
የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም ያረፉት ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በ1980 ዓ.ም ነሐሴ 29 ቀን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ፓትርያርክ ተብለው የተሾሙ ሲሆን ላለፉት 34 አመታት በፓትርያርክነት አገልግለዋል።
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የቤተክርስቲያኗ ትምህርት የሆኑትን አቋቋም፣ ድጓና ዝማሬ መዋስዕት በላቀ ሁኔታ የተማሩ መሆናቸውን ከሕይወት ታሪካቸው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።