የኢትዮጵያ ሰላም፣ ሉዓላዊነትና እድገት ለቱርክ እጅግ አስፈላጊ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰላም፣ ሉዓላዊነትና እድገት ለቱርክ እጅግ አስፈላጊ ነው
መጋቢት 2/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ሰላም፣ ሉዓላዊነትና እድገት ለቱርክ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን የቱርክ-ኢትዮጵያ ፓርላማ ወዳጅነት ቡድን ሊቀ-መንበርና የቱርክ ፍትህና ልማት ፓርቲ ተወካይ መህመት ሳይት ኪራዞግሉ ገለጹ።
126 ዓመት ያስቆጠረው የቱርክና ኢትዮጵያ ግንኙነት በዘመናት ሂደት ከፍ ወዳለ ደረጃ መድረሱንም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን የጀመሩበትን 125ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ባለፈው ዓመት ማክበራቸውን አስታውሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ዓመት በቱርክ አፍሪካ ጉባኤ ላይ በመታደም የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የሚያጠናክሩ ምክክር ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰላም፣ ሉዓላዊነትና እድገት ለቱርክ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ይህንኑ ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ቱርክ እንደምትደግፍ ጠቁመዋል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በፖለቲካ መስክ ያላቸው ግንኙነት በፈጣን ሁኔታ እያደገ መጥቷል ብለዋል፡፡
ቱርክ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ካላት ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ከፍተኛው ሀብት በኢትዮጵያ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ቱርክ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
የቱርክ ፕሬዚዳንትና የፓርቲው ሊቀመንበር ረሲፕ ጣይፕ ኤርዶጋን ያስተላለፉትን የደስታ መግለጫ በዚሁ ወቅት አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ የኡጋንዳ ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት ተወካይ ኢልፔር ሲሞን ፒተር ፓን አፍሪካኒዝም የአህጉሪቱን ህዝቦች ሰላም ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፓን አፍሪካኒዝም፣ አርበኝነት፣ የዴሞክራሲ፣ ማህበራዊና የኢኮኖሚ ዕድገት ለአፍሪካ ህዝቦች መጻኢ እድል ማማር ወሳኝ በመሆኑ በትኩረት እንስራበት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ገጥሟት በነበረው ፈተና ሳትበገር በጽናት መከራውን እንድትሻገር ያደረጉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አድንቀዋል፡፡
ሁለቱ ፓርቲዎች ያላቸውን አብሮነት በተጠናከረ ግንኙነት ከፍ ማድረግ ከቻሉ የአፍሪካውያንና የህዝባቸውን ብልጽግና ማረጋገጥ ይችላሉ ብለዋል፡፡
አጋርነታችንን በአቅም ግንባታ፣ በንግድና በፖለቲካ ዘርፍ በማሳደግ አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን በማለት የፓርቲያቸውን አቋም አሳውቀዋል፡፡
ተወካዩ የፓርቲው ሊቀመንበርና የኡጋንዳ ፕሬዚዳንት ዩሪ ሙሴቪኒን የደስታ ምኞት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡