ምርትን በመደበቅ የኑሮ ጫና እንዲፈጠር በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ምርትን በመደበቅ የኑሮ ጫና እንዲፈጠር በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል
መጋቢት 02/2014 (ኢዜአ) ምርትን በመደበቅ በኅብረተሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እንዲፈጠር በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ገለጸ።
የቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ሚኤሳ፤ በመዲናዋ ምርትን በመደበቅ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸው ተደርሶበታል ብለዋል።
ይህንን ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለማስቆም የቁጥጥር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ፤ የተለያዩ አደረጃጀቶች ተዋቅረው የቁጥጥር ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ግብረ ኃይሉ ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን፣ ደረሰኝ አልባ ንግድን፣ ምርት መደበቅንና በሌሎች ያልተገቡ የንግድ አዝማሚያዎች ላይ ሰፊ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት የኅብረተሰቡን ፍላጎት እየተፈታተነ ያለውን የዘይት ፍላጎት በማባባስ ምርቱን ደብቀው የነበሩ አካላት ተይዘው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተደረገው የቁጥጥር ሥራ ከ450 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት መያዙን ጠቁመው ይህም በተመጣጣኝ ዋጋ በሸማቾች በኩል ለኅብረተሰቡ እንደገና እየተከፋፈለ መሆኑን ጠቁመዋል።
በተጓዳኝም ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ የተሳተፉ አንዳንድ የችርቻሮ መሸጫ ሱቆችም መታሸጋቸውን ጠቁመዋል።
ግብረ ኃይሉም ምርትን በመደበቅ በማኅበረሰቡ ላይ የኑሮ ጫና እንዲፈጠር በሚያደርጉ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ምርትን በመደበቅና በሌሎች ያልተገባ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ በመሰማራት የኅብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ ላይ ጫና የሚሳድሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።
ምርትን በመደበቅና በሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተሰማሩ አካላትን በማጋላጥና ጥቆማ በመስጠት ኅብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
ከኦሮሚያና ከሌሎች ክልሎች አርሶ አደሮች፣ አምራቾችና ሸማች ማኅበራት ጋር ትስስር በመፍጠርም በመዲናዋ እየተባባሰ ያለውን የኑሮ ጫናውን ለማቃለልም እየተሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።