ቀጥታ፡

ባንኩ 12ኛውን ይቀበሉ ያሸንፉ የሎተሪ ዕጣ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ ግንቦት 10/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 12ኛውን 'ይቀበሉ ያሸንፉ' የውጭ ምንዛሪ ማበረታቻ የሽልማት ስነ-ስርዓት አካሄደ። ዛሬ የወጣው ዕጣ ከመጋቢት 1 ቀን እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2010 ዓም ድረስ በባንኩ ምንዛሪ የፈጸሙ ሰዎችን የሚያካትት መሆኑ ተጠቅሷል። በአንደኛው ዕጣ 12 ሰዎችን የሚጭን ዘመናዊ ሚኒ ባስ፣ በሁለተኛው ዕጣ 16 ፍላት ስክሪን ቴሌቭዥኖችና በሶስተኛው ዕጣ 32 ዘመናዊ  ተንቀሳቃሽ ስልኮች ለዕድለኞች ቀርበዋል። አንደኛውን ዕጣ የሻሸመኔ ቅርጫፍ ደንበኛ ማሸነፋቸው የተገለጸ ሲሆን የዕጣው ቁጥርም 6342442 ሆኗል። የባንኩ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በልሁ ታከለ እንደገለጹት ፕሮግራሙ ከተጀመረ ሶስት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን በየዓመቱ ከአዲስ አመት፣ ገና፣ ፋሲካና ኢድ አልፈጥር በዓላት ጋር ተያይዞ እየተካሄደ ይገኛል። ይህም ህብረተስቡ በህጋዊ መንገድ ገንዘቡን እንዲመነዝር በማድረግ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ማሳደጉን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ባንኩ ባሉት ከ1 ሺህ 260 በላይ ቅርንጫፎች ዓለም አቀፍ የሀዋላ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 13ኛው ዙር የውጭ ምንዛሪ ማበረታቻ የሽልማት ፕሮግራም የረመዳንን ፆምና የኢድ አልፈጥር በዓልን ታሳቢ በማድረግ ከግንቦት 15 እስከ ሀምሌ 14 ቀን 2010 ዓም ባለው ጊዜ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም