የቱርኩ ገዥ ፓርቲ (AKP) አመራሮች በብልፅግና ጉባኤ ለመታደም አዲስ አበባ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የቱርኩ ገዥ ፓርቲ (AKP) አመራሮች በብልፅግና ጉባኤ ለመታደም አዲስ አበባ ገቡ
አዲስ አበባ መጋቢት 2 / 2014 ዓ.ም / ኢዜአ/ የቱርክ ገዥ ፓርቲ የሆነው የፍትህና ልማት ፓርቲ (AKP) የውጭ ጉዳይ ዘርፍ ምክትል ሊቀመንበር ፌቭዚ ሻንቬርዲና የቱርክና ኢትዮጵያ ወዳጅነት ቡድን ኃላፊ መህመት ሳይት ኪራዞግሉ በብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ ለመታደም አዲስ አበባ ገብተዋል።
እንግዶቹ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል አምባሳደር ደመቀ አጥናፉ አቀባበል አድርገውላቸዋል ።
የቱርክ ገዥ ፓርቲ የሆነው የፍትህና ልማት ፓርቲ (AKP) የውጭ ጉዳይ ዘርፍ ምክትል ሊቀመንበር ፌቭዚ ሻንቬርዲ በብልፅግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ ለመታደም መምጣታቸውን እንዳስደሰታቸው ገልጸው ኢትዮጵያና ቱርክ የጠበቀ ሁለንተናዊ ግንኙነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
ሁለቱ አገሮች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠረ ጠንካራ ባለ ብዙ ዘርፍ ግንኙነት እንዳላቸውና ቱርክ በኢትዮጵያ ሰፊ ኢንቨስትመንት ካላቸው ሀገራት አንዷ መሆኗን አውስተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን በበኩላቸው ኢትዮጵያና ቱርክ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አስታውሰው ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ በኢኮኖሚው ዘርፍም ግንኙነታቸው በጣም እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል።
እ.አ.አ በ2001 ከተለያዩ ከቱርክ ፓርቲዎች በተውጣጡ ፖለቲከኞች የተመሰረተው የቱርክ የፍትህና ልማት ፓርቲ (ኤኬ ፓርቲ) ከፈረንጆቹ 2003 ጀምሮ ቱርክን እየመራ የሚገኝ ፓርቲ ሲሆን፤የፓርቲው መሪ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ናቸው።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካን ቡድናቸው ባለፈው 2013 ነሐሴ ወር በቱርክ አንካራ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቱርክ የተደረገላቸው አቀባበልም የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የሚያንፀባርቅና ሞቅ ያለ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉብኝታቸውን አጠናቅቀው ሲመለሱ "የቱርክ መንግሥት እና ሕዝብ ያደረገልንን የወሳኝ ጊዜ ትብብር ሀገራችን ኢትዮጵያ መቼም አትረሳውም" ብለው ነበር።
የመሪዎቹን ውይይት ተከትሎ በቱርክ ሁለቱ ሀገራት የወታደራዊ ስምምነት ማድረጋቸው ይታወቃል።
የቱርክ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን በ2007 ዓ.ም ኢትዮጵያን መጎብኘታቸው ይታወቃል። በጉብኝታቸውም በወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በሁለትዮሽና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው ነበር።
ቱርክና ኢትዮጵያ ይፋዊ የሆነ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩበትን 125ኛ ዓመት መታሰቢያ ባለፈው ዓመት ማክበራቸው ይታወሳል።
ቱርክና ኢትዮጵያ መደበኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት በፈረንጆቹ 1896 ሲሆን ቱርክ የመጀሪያውን ቆንፅላ ፅህፈት ቤቷን በሀረር ከተማ በፈረንጆቹ 1910 ከፍታ ነበር።
ከሁለት ዓመታት በኋላ በ1912 ቱርክ በአዲስ አበባ ቆንፅላ ፅህፈት ቤት ስትከፍት የሀረሩን ወደ ክብር ቆንፅላ ፅህፈት ቤት ዝቅ አድርጋዋለች። የአዲስ አበባው ቆንፅላ ፅህፈት ቤት በ1926 ወደ ኤምባሲነት አደገ። ኢትዮጵያም በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ መሪነት ኤምባሲዋን በ1933 በቱርክ ከፈተች።
ንጉሡም ሁለት ጊዜ ቱርክን ጎብኘተዋት ነበር።
ቱርክና ኢትዮጵያ በደርግ ዘመን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እስከመቋረጥ ደርሶ የነበረ ሲሆን፥ ከደርግ መውደቅ በኋላ ግንኙነታቸውን እንደገና በመጀመር ኢትዮጵያም ዘግታው የነበረውን ኤምባሲዋን በፈረንጆቹ 2006 ዳግም ከፍታለች።