በብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ የህዝብን አደራ በብቃት የሚወጡ ጠንካራ አመራሮች የሚመረጡ ይሆናል - ኢዜአ አማርኛ
በብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ የህዝብን አደራ በብቃት የሚወጡ ጠንካራ አመራሮች የሚመረጡ ይሆናል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) በብልጽግና ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ የህዝብን አደራ በብቃት የሚወጡ ጠንካራ አመራሮች የሚመረጡ መሆኑን ፓርቲው አስታወቀ፡፡
የፓርቲው የህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ፤ በነገው እለት መካሄድ የሚጀምረውን የፓርቲውን መጀመሪያ ጉባኤ በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም ብልጽግና ፓርቲ በርካታ ታሪካዊ ሂደቶችን አልፎ በወሳኝ ወቅት የተወለደ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን የነፃነት፣ እኩልነትና የሰብዓዊ መብት ጥያቄ በአደባባይ በግለጽ በጀመሩበት ወቅት የተመሰረተው ብልጽግና ኢትዮጵያን ከብተና ስጋት ታድጓል ብለዋል፡፡
የህዝቦች የነጻነትና እኩልነት መብታችን ይከበርልን ጥያቄ ሲቀነቀን ወጣቶች መስዋዕትነት ሲከፍሉ በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ አመራሮችም ንቅናቄውን ተቀብለው እንደነበር አውስተዋል፡፡
የኢህአዴግ ፓርቲ ሲከስም በኢትዮጵያ ሁሉንም ያካተተ፣ ተራማጅና እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታን መርህ ያደረገው ብልጽግና መመስረቱን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት የተደረጉ የሪፎርም እርምጃዎች ኢትዮጵያን ከብተና ያዳኑ ነበሩ ያሉት ዶክተር ቢቂላ፤ ለዴሞክራሲ ስርዓት ልምምድ የሚሆኑ ተቋማት ተገንብተዋል፤ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችሉበት አውድ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፖለቲካ "አጋር" እየተባሉ አገር የመምራት ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ተደርገው የቆዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን በማቀፍ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲጎለብት በማድረግ አሳታፊነቱን በተግባር አረጋግጧል ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ምድር አንድነት ተፈጥሯል፤ ኢኮኖሚውን ከውድቀት በመታደግ አበረታች ውጤት አስመዝግቧልም ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ አገራዊ እሳቤዎች እንዲጎለብቱ፣ በህብረ ብሔራዊነት ውስጥ ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚቻል አሳይቷልም ብለዋል ዶክተር ቢቂላ፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃይል በማመንጨት ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን በራሷ አቅም መገንባት እንደምትችል ያሳየው የለውጡ አመራር ከመጣ በኋላ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በጉባኤው የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የአስተሳሰብ አንድነት በመፍጠር በጋራ የሚሰሩበትን አሰራር ለመፍጠር እንደሚመክር ጠቅሰዋል።
ጉባኤው የህዝብን አደራ በብቃት የሚወጡ ጠንካራ አመራሮች የሚመረጡበት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ነገ በሚያካሂደው ታሪካዊ ጉባኤም በተለያዩ ዘርፎች የታዩ ተስፋዎችና ድክመቶች ተገምግመው የመፍትሄ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት፤ ፓርቲው ለህዝብ የገባውን ቃል የሚወስንበት ታሪካዊ ዕለት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በአዳማ ከተማ በተደረገው የቅድመ ጉባኤ ውይይትም አባላት ባህላቸውን እንዲለዋወጡና በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ በጥልቀት ተወያይተው ለጉባኤው ግብዓት የሚሆን ሃሳብ ያቀረቡበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼