በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

73

መጋቢት 1/2014 (ኢዜአ) በህገ ወጥ መንገድ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋውሩ የተገኙ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የአምቦ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኮማንደር ሲሳይ ሂርጳ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ መነሻውን አሶሳ በማድረግ ሶስት መትረየሶችን ወደ ምእራብ ሸዋ ዞን ጊንጪ ከተማ ሲያጓጓዙ በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ግለሰቦቹ መሳሪያዎቹን የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 -37618 ኦሮ በሆነ የቤት ተሽከርካሪ ጭነው ለማሳለፍ ሲሞክሩ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

በተሽከርካሪው የነዳጅ ታንከር ላይ ሌላ ብረት በመበየድ መትረየሶቹን ፈታተው በመደበቅ ወደ ጊንጪ  በማጓጓዝ ላይ እንዳሉ  ትናንት በአምቦ አዋሮ ኬላ በተደረገ ፍተሻ መያዛቸውን አመልክተዋል ።

በጉዳዩ ላይ ቀደም ብሎ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በብሔራዊ መረጃና ደህንነትና በአምቦ ከተማ ፖሊስ ትብብር በተካሄደ የተቀናጀ የክትትል ስራ ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን  ለመቆጣጠር በሚደረገው ጥረት ትብብሩን እንዲያጠናክር ኮማንደር ሲሳይ ሂርጳ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም