ቀጥታ፡

"ከፈተና ወደ ልዕልና“የብልጽግና አዲሱ መንገድ

በህዝብ እምቢተኝነት ማዕበል የተፈተነው ኢሕአዴግ "ራሴን በጥልቅ አድሻለሁ“ ቢልም የጭቆና ቀንበር ያንገሸገሸውና የስርዓት ለውጥን የሻተው ህዝባዊ ተቃውሞ በመላ አገሪቷ እየሰፋ፣ ለውጥ የሻቱ የፓርቲው አመራሮችንም እያበዛ ቀጠለ።

በኢህአዴግ 11ኛው ጉባኤ ዶክተር ዐቢይ አህመድ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ውህደትን ለማከናወን ሲወስን ከአራቱ አባል ድርጅቶች አንዱና የስርዓቱ አዛዥና ናዛዥ ከነበረው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ/ሕወሃት በስተቀር ቀሪዎቹ ውህደት ፈጸሙ።

ለ27 ዓመታት በአጋርነት ስም ተቆጥረው በአገራቸው ማህበረ-ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ዕድል ተነፍጓቸው የነበሩ የየክልሉ ገዥ ፓርቲዎችም የውህደቱ አካል ነበሩ።

በውህደት የተመሰረተው አዲሱ ፓርቲ ‘ብልጽግና’ በሚል ስያሜ በኢሕአዴግ ምክር ቤት መጽደቁም ይፋ ሆነ፤ በደም አሻራው ውድ ህይወቱን የሰጠው ህዝብም ሀገሩ ወደ ለውጥ ጎዳና እንድታመራ በር የከፈተ አማራጭን ፈጠረ።

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ከ27 ዓመታት በላይ በተሻገረ የህወሃት መራሹ የኢሕአዴግ መንግስታዊ ስርዓት የውንብድና አገዛዝ ተፈትነዋል።

ዜጎች የጭቆና ቀንበር እንዲጫንባቸው፤ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊትና ግፎች የዕለታዊ ኑባሬያቸው ዕጣ እንዲሆኑ ተደርጓል፤ ድሃዋ ኢትዮጵያም መቀነቷ ተበዝብዞ ጥሪቶቿ ተዘርፏል።

ይህ የጭቆናና የግፍ አገዛዝ ያንገሸገሸው ህዝብ ግን ውሎ አድሮ ስርዓቱን ገርስሶ ነጻነቱን ለመቀዳጀት ተነሳ። ግንባሩን ለጠበንጃ ሰጥቶ፣ እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅና እምቢተኝነት እያደረገ ስርዓቱን መገዳደር ቀጠለ።

በህዝብ እምቢኝነት ማዕበል የተፈተነው ኢሕአዴግም "ራሴን በጥልቅ አድሻለሁ“ በሚል የውንብድና አገዛዙን ለማሻሻል ቃል ቢገባም ቅሉ ለዘመናት የጭቆና ቀንበር ያንገሸገሸው አገሬው እምቢተኝነቱን አልገታም ነበር።

በአራት እህት ድርጅቶች የተዋቀረው ይህ ገዥ ፓርቲ የመግለጫ ጋጋታ ቢያበዛም የስርዓት ለውጥን የሻተው ህዝባዊ ተቃውሞ በመላ አገሪቷ እየሰፋ፣ ለውጥ የሻቱ የፓርቲው አመራሮችን ቁጥር እያበዛ ቀጠለ።በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረው የለውጥ ሃይል እየገፋ፣ ህዝባዊ እምቢተኝነትና ጫና እየበረታ በመጣበት ወቅት በኢህአዴግ 11ኛው ጉባኤ ዶክተር ዐቢይ አህመድ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ።

ከ5ኛው መደበኛ ጉባኤ ጀምሮ ሲነሳ የቆየው የኢህአዴግ የውህደት ጉዳይም ከ11ኛው መደበኛ ጉባዔ በኋላ ወደ ፈጣን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ገባ።በጊዜ ሂደትም የኢህአዴግ ምክር ቤት ውህደትን ለማከናወን ሲወስን ከአራቱ አባል ድርጅቶች አንዱና የስርዓቱ አዛዥና ናዛዥ ከነበረው ሕወሃት በስተቀር ቀሪዎቹ ውህደት ፈጸሙ።

ውህደቱም የሶስቱ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለ27 ዓመታት በአጋርነት ስም እንደ ሶስተኛ ወገን ተቆጥረው በአገሪቱ ማህበረ-ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ዕድል ተነፍጓቸው የነበሩ የየክልሉ ገዥ ፓርቲዎችም ታቅፈዋል።ሕግና ስርዓትን ተከትሎ በውህደት የተመሰረተው አዲሱ ውህድ ፓርቲ ‘ብልጽግና’ የሚል ስያሜ በኢሕአዴግ ምክር ቤት መጽደቁም ይፋ ሆነ።

በደም አሻራው ውድ ህይወቱን የሰጠው ህዝብም ሀገሩ ወደ ለውጥ ጎዳና እንድታመራ በር የከፈተ ሁነኛ አማራጭን ፈጠረ።መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመረጡት ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአገር ውስጥና በውጭ አገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ ተችሯቸው የለውጥ ስራቸውን ጀመሩ።

አገራዊ ለውጡ መሰረት እንዲይዝ የሚያስችሉ ተቋማዊና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ማከናወን ቀጠሉ።ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በባህል፣ በብዝሀነት እና በስልጣኔ የነበራትን ቀደምት ክብርና ከፍታ በወንድማማችነትና ትብብር ላይ በተመሰረተ መርሆ ለመመለስ የጀመሩት ስራ የብዙሃኑን ቀልብ ሳበ።

በክፋት፣ ጥላቻና ቂም በቀል በተካኑት የሕወሃት ፖለቲከኞች ሴራና የአክራሪ ብሔርተኞች ጫና እየተፈተነም ቢሆን የኢትዮጵዊነት መንፈስ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ተቀጣጠለ።

አገራዊ ለውጥ የማይሹ የጨቋኝና በዝባዥ ቡድን አባላትም በቀደመ የጥፋት ሰንሰለታቸው ተጠቅመው ለዘመናት በደም ተዛምዶና ተባብሮ በኖረው ህዝብ መካከል ግጭት፣ መፈናቀልና ግድያ እንዲፈጠር የእጅ አዙር እኩይ ስራቸውን ተያያዙት።

ከአራት ኪሎ ወደ መቀሌ በህዝብ የተገፋው የህወሃት ቡድን እኩይ ግብሩን አጠናክሮ ተስፋ የተጣለበትን ለውጥ ቀልብሶ ወደስልጣን የመመለስ ምኞቱን ለማሳካት ይፋዊ እንቅስቃሴውን ቀጠለ።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ለአስርት ዓመታት በቀበሮ ጉድጓድ ተወሽቆ ትግራይን ህዝብ ሲጠብቅና ሲያለማ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሲያስከበር በኖረው የሰሜን ዕዝ ላይ ለጆሮ የሚከብድ አሰቃቂ ጥቃት ፈጸመ።

በመከላከያ ሰራዊት ዕዞች መካከል በትጥቅ አቅሙ ከፍተኛ የሆነውን ሰሜን ዕዝ በክህደት አጥቅቶ ወደ አራት ኪሎ ለመመለስ ያቀደው ቡድን ግን ህልሙ ከንቱ ቅⶰት ከመሆን አላለፈም።በመላው ኢትዮጵያዊያን ትብብር በተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላም በህልውና ዘመቻው የሉዓላዊነት አደጋ በእልህ አስጨራሽ ተጋድሎና መስዋትነት ተቀለበሰ።

ከጅምሩ በፈተና የታጀበው የለውጡ አመራርም ውስጣዊና ውጫዊ የበሬ ወለደ ፕሮፖጋንዳና መልከ ብዙ ጫና ሳይበገር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ መስኮች ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝግቧል።

አገሪቷ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የውጭ ታዛቢዎች በፍትሃዊነትና ገለልተኛነቱ የመሰከሩለት፣ ኢትዮጵያዊያን በነቂስ ወጥተው ድምጻቸውን የሰጡበት 6ኛው ዙር አገራዊ ምርጫም በስኬት ተከወነ። ኢሕአዴግን አፍርሶ በአዲስ ውህደት የተመሰረተው ብልጽግና ፓርቲም በምርጫው አሸናፊ ሆነ።

በምጣኔ ሃብት ረገድም የኢትዮጵያዊያን የሰንደቅ ዓላማ ፕሮጀክት የሚሰኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውስብስብ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ ለአቅመ ሃይል ማመንጨት በቃ።በቱሪዝም መዳረሻ ልማት በኩል በገበታ ለሸገር የተጀመሩት የወዳጅነት አደባባይ፣ እንጦጦና አንድነት ፓርኮች በአስደናቂ ፍጥነት ተመረቁ፤ በገበታ ለአገር የታቀፉ ፕሮጀክቶች ክዋኔም ተጀመረ።

በኢኮኖሚና ማህበራዊ መስክ ሰፊ ፋይዳ ያላቸው በርካታ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ግንባታዎችም ለፍጻሜ ደርሰዋል።እነኚህ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ስኬቶች ቢመዘገቡም ዳሩ ዛሬም ኢትዮጵያ ከመልከ ብዙ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች አልተላቀቀችም።

ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ማለትም ጦርነት፣ ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የኑሮ ውድነት፣ ድርቅ፣ … ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን እየፈተኑ ቀጥለዋል።ገዥው ፓርቲ ብልጽግናም በስኬቶችና ፈተናዎች መካከል ሆኖ ጠቅላላ ጉባኤውን ለማድረግ ዋዜማው ላይ ይገኛል።

ኢትዮጵያ እጅግ በውስብሰብ አገራዊ ፈተናዎች አጣብቂኝ ውስጥ በመሆኗ ከገዥው ፓርቲ ብልጽግና ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ የሚወጡ ውሳኔዎች የአገሪቷን መጻዒ ዕድሎች ይወስናሉና አገር ከጉባዔው ብዙ ትጠብቃለች።

ከሁሉም ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የአገሪቷን ሕልውና ማስቀጠልና የዜጎችን ሰላምና ደህንንት ማረጋገጥ መሆኑ አይቀርም። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁት ሕወሃትና ሸኔን ጨምሮ በየአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች የአገሪቷን ሕልውና እየተፈታተኑ በመሆኑ የአገር ሕልውናን ለማረጋገጥ በምን መልኩ ይሰራል የሚሉ ውሳኔዎች ከጉባዔው ይጠበቃሉ።

ሚሊየኖች በተፈናቀሉበትና ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየተባባሱ በመጡበት በዚህ ወቅት የገዥው ፓርቲ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ መግባት፣ በሕይወት የመኖር ዋስትና፣ የመንቀሳቀስ፣ ሀብትና ንብረት አፍርቶ የመኖር መብቶቻቸውን ማረጋገጥ የመንግስት ግዴታ በመሆኑ ግዴታውን ለመወጣት የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንዲኖሩም ህዝብ ብዙ ይጠብቃል።

የዜጎችን ማህበረ ምጣኔ ሃብታዊ የኑሮ መደላድል ፈተና ውስጥ የጣለውን ጅምላ ግድያ፣ መፈናቀልና ማህበራዊ እረፍት መንሳትም አፋጣኝና መንግስታዊ ምላሽ መስጠት አጽንኦትን ይሻል።በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸደውን ዜጎች በዘላቂነት መልሶ ማቋቋምና ጊዜያዊ ድጋፎችን ተደራሽ የማድረግ እርምጃዎችን ከማጠናከር አኳያም ጉባኤው አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ መንበረ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው የሚያቀነቅኑት አገርን በጽኑ መሰረት ላይ የማንበር ግብ ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። የተስተካከለ የፖለቲካ ስርዓትን መዘርጋት፣ በህብረ ብሔራዊነት ላይ የተመሰረተ የዴሞክራሲ ስርዓት መፍጠር፣ ብዝሃነት የግጭትና የፉክክር ሳይሆን ጌጥና የአብሮነት መገለጫ የሆነበት ማህበረ ኢኮኖሚ በመገንባት ዜጎችን ወደ ከፍታ ማሸጋገር ይገባል።

የኢትዮጵያዊያንን አንድነት ማጎልበት፣ ታሪካዊና ባህላዊ መስተጋብር ማስቀጠል፣ በታሪክ መወራረስ እርሾን የነገ አብሮነት እሴትነት መጠቀም፣ የጥል ግድግዳን አፍርሶ የፍቅር ድልደይ መገንባት፣ ዘላቂ ህዝባዊ ተግባቦትን ማጠናከር ያሻል።

በተለይም ኢትዮጵያ ለምታካሂደው አገራዊ ምክክር መድረክ እነዚህን እሴቶች ተጠቅሞ ውጤታማ አገራዊ መግባባት የመፍጠር፣ አስተማማኝ ሰላምና ደህንነት የሰፈነባት አገር መገንባት የትኩረት ነጥቦች እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ለነዚህ ግቦች እውን መሆን የገዥው ፓርቲ ብልጽግና ሃላፊነት ከፍተኛ በመሆኑ በጉባኤው የቤት ስራዎችን በሚገባ ለመከወን አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል። ይህም ውስጣዊ አገራዊ አንድነትን ለማጠናከር ተራማጅ ሃሳቦችን ለማፍለቅ ምቹ መደላድል ለመፍጠርም አስፈላጊ ይሆናል።

በርግጥ የብዝሃ ልሳን፣ የቱባ ባህል፣ ታሪክ፣ እምነት እና የሕብረ ብሔራዊነት ካስማ፣ ከዳሎል እስከ ራስ ደጀን አስደናቂ መልክዓ ምድራዊ ድንቅ ተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤቷ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና ትሻለች።ፀጋዎቿን አልምታ ዜጎቿን ፍሬ ማቋደስ፣ በድህነት አረንቋ የሚማቅቁ ዜጎቿን ተጨባጭ የኑሮ ሁኔታ መለወጥ የመንግስት ሃላፊነት ነው፤ የወቅቱ መንግስት ደግሞ ብልጽግና ነው።

ግብርናውን በማዘመን ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን አርብቶ አደርና አርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል አገራዊ ፖሊሲዎች ቀርጾ መተግበር ይጠይቃል። ጭስ አልባ ኢንዳስትሪ የሚሰኘውን የቱሪዝም መስክ ማልማትና ማስተዋወቅ አገራዊ ገቢን ማሳደግ ብርቱ ስራ ይጠይቃል።

የአምራች ዘርፉ እምርታዊ እድገት አስመዝግቦ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ማፋጠን፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማትና የፕሮጀክቶች ማኔጅመንት አቅምን ማጎልበት እና ሌሎችም አይነት የዘላቂ ልማት ግቦችን እውን መሬት ላይ ማውረድ ተገቢነቱ አጠያያቂ አይደለም።

ድርቅና ጎርፍ መሰል የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም የሚያስችሉ ጊዜያዊና ዘላቂ እርምጃዎች ለመውሰድ የሚያስችል ውሳኔም ይጠበቃል። በተለይም በዚህ ወቅት በተወሰኑ ክልሎች ሚሊዮኖችን ለመልከ ብዙ ማህበራዊ ቀውስ የዳረገው ድርቅ የሚያደርሰውን ጉዳት የመቀነስ አስቸኳይ የመፍትሔ እርምጃዎች እንደሚያስፈልጉም እሙን ነው።

በየጊዜው በሚንረውና ሰሞነኛም አጀንዳ በሆነው የኑሮ ውድነት ጉዳይ አልባት መስጠትም ሌላው ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነው።በዲፕሎማሲው ዘርፍም ብዙ ይጠበቃል። ኢ-ተገማች በሆነው የዓለም ኅይላት አሰላለፍ ባለበት በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ብልጠትና ብልሃት የተሞላበት አረማምድ ያሻታል።

ለዚህ ደግሞ ለሙያው ብቃትና ዕውቀት መርህ ላይ የተመሰረተ፣ የየወቅቱን የዓለምን አዝማሚያ ተንትኖ የሚሰራ አደረጃጀትና አሰራር መዘርጋት ይጠይቃል። የኢትዮጵያን እጅ በመጠምዘዝ ሀብቶቿን ተጠቅማ እንዳትበለጸግ የሚደረጉ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጫናዎችን ተቋቁሞ የውጭ ሃይላትን ፍላጎቶች የማክሸፍ፣ የአገር ክብርና ሉዓላዊነትን የማስከበር አማራጭ የዲፕሎማሲ ፍኖት ያስፈልጋል።

ለዚህ ደግሞ ገዥው ፓርቲ በጠቅላላ ጉባዔው አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ ይጠበቅበታል። ከመጋቢት ሁለት እስከ አራት ቀን 2014 ዓ.ም ከፈተና ወደ ልእልና በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ በበርካታ አገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግ በህዝብ ትብብር ተግባራዊ የሚሆኑ በርካታ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። በፈተና የታጀበውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ደግሞ ፓርቲው የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች በርብርብ ወደ ውጤት መቀየር ያሻል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም