የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ለሦስተኛ ጊዜ እውቅና አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ለሦስተኛ ጊዜ እውቅና አገኘ
አዲስ አበባ መጋቢት 01/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን በመድኃኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ባስመዘገበው ስኬት ለሦስተኛ ጊዜ እውቅና አገኘ።
በመድሃኒት አምራች፣ አስመጪዎችና ላኪዎች እንዲሁም ጅምላ አከፋፋዮች ላይ በሚደረገው የቁጥጥርና የክትትል ሥራ ባስመዘገበው ውጤት ያገኘው እውቅና መሆኑም ተገልጿል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሄራን ገርባ፤ ከዚህ ቀደም በሁለት ዘርፎች ሁለት ዓለምአቀፍ እውቅናዎችን ማግኘቱን አስታውሰዋል።
አሁንም በመድኃኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ባስመዘገበው ስኬት ለሦስተኛ ጊዜ እውቅና ማግኘቱን ገልጸዋል።
ለባለሥልጣኑን እውቅናውን የሰጠው የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ሲሆን በኢንስፔክሽን አሰራር በISO/IEC/17020/2012 መሆኑን ጠቅሰው ለአምስት ዓመታት የሚያገለግል ሲሆን በየዓመቱ የሚታደስ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
የአሁኑ ሽልማት በቁጥጥር ሂደቱ ማህበረሰቡ ይበልጥ እምነት እንዲያሳድር የሚያደርግና የመድኃኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ውጤት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
በአገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማጎልበት የሚረዳና በተለያዩ አገራት የገበያ ተፈላጊነታቸውን ለመጨመር ተቀባይነታቸውን የሚያሳድግ እንደሚሆንም አብራርተዋል።
በተለያዩ የንግድ ትስስሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ተሳታፊ በመሆኗ በተለይም ለአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ያግዛልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አርአያ ፍስሃ፤ በፍተሻ ላቦራቶሪና በህክምናው ዘርፍ ለተሰማሩ እንዲሁም በኢንስፔክሽን ዘርፍ የአክሬዲቴሽን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው ከ100 በላይ ለሆኑ ተቋማት አክሬዲቴሽን መሰጠቱንና አገልግሎቱ ባደረገው የክትትል ፍተሻ ከ30 በላይ የሆኑ ተቋማት አክሬዲቴሽናቸውን መነጠቃቸውንም ተናግረዋል።
አክሬዲቴሽን ዳግም ፍተሻን በማስቀረት ንግድን የሚያቀላጥፍ መሆኑንና አገልግሎት ፈላጊዎች አክሬዲቴሽን በአገር ውስጥ ማግኘታቸው ለአገልግሎቱ ያስፈልጋቸው የነበረውን የውጭ ምንዛሪን የሚያስቀር መሆኑንም ገልጸዋል።
ተቆጣጣሪ አካላትም በተረጋገጠ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲሰጡ የሚያስችልና ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ፤ የጤናውን ዘርፍ ተደራሽነት ለማስፋት ባለፉት ሦስት ዓመታት የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የጤናውን ዘርፍ የልማት እቅድ ለማሳካት ማሻሻያና ቁጥጥር ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢንስፔክሽን ሥራው አክሬዲትድ መሆን ለሚያከናውነው ተግባር መሰረታዊ ጉዳይ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
ከምግብና መድኃኒት ጋር ተያይዞ የሚጠበቁ የጥራት ውጤቶችን ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።