በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በሁለቱም አገራት በኩል ፍላጎት ታይቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በሁለቱም አገራት በኩል ፍላጎት ታይቷል
መጋቢት 1 2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያና አሜሪካ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር በሁለቱም አገራት በኩል ፍላጎት መኖሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ዲና በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ክንውኖች ላይ በማተኮር በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ አሜሪካ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ለላከቻቸው ጉዳይ ፈጻሚ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን፤ በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ እስረኞችን መፍታቷን፣ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሟንና አሸባሪው ህወሓት በአፋር ወሰን አካባቢ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርሰ እየከለከለ መሆኑን ማስረዳት ተችሏል ነው ያሉት።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፤ ከአምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን ጋር ባደረጉት ውይይት የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጎልበት ከሁሉም ወገን ግልጽ ፍላጎት እንዳለ ገልጸዋልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም የእውነትና ትክክለኛ መንገድ መሆኑን ለዓለም ለማስረዳት በአምባሳደሮቿና ቆንስላ ጄነራሎቿ በኩል ማብራሪያ እየሰጠች መሆኑንም ያመለከቱት አምባሳደር ዲና በዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት እንደሌለ ለሊባኖስ መንግስት ማብራሪያ መሰጠቱን አስታውሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በአረብ ሊግ በኩል የሚታየውን የተሳሳተ አቋም በአረብ ሊግ አባሏ ሊባኖስ በኩል ለማስረዳት ጥረት መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ከጎረቤት አገራት ጋር በመልካም ትብብር እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያና ኤርትራ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ለዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ግጭት በሰላም ተፈትቶ ሁለቱ አገራት በቀጣናው ሰላም ከማስፈንም ባለፈ በተለያዩ መድረኮች እርስበርስ እየተደጋገፉ መሆኑንም አብራርተዋል።
የሩሲያና ዩክሬን ግጭት የዓለም ስጋት መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ዲና፤ ይህንን አስጊና አውዳሚ ጦርነት ኢትዮጵያም በጥንቃቄ ትመለከተዋለች ብለዋል።
የሁለቱን አገሮች ውጊያ በተመለከተ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ስብሰባ ላይ በተሰጠው ድምጽ ኢትዮጵያ ያልተገኘችው ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ስለምትሻ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚኖራትን ተሰሚነት ከፍ ለማድረግ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላትን በማስፋት በኩል በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የከፈቷቸው ማእከላት መጠናከር ይኖርባቸዋል ብለዋል።