ቀጥታ፡

የንግድና ቢዝነስ ሃሳባቸው በፈጠራ ማዕከል ድጋፍ ለስኬት የበቁ ወጣቶች

አዲስ አበባ መጋቢት 01/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፈጠራ ማዕከል የንግድና ቢዝነስ ሐሳባቸው ወደ ተግባር እንዲለወጥ ያስቻላቸው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ሥራ ፈጣሪ ወጣቶች ገለጹ።

በኢትዮጵያ በርካታ ወጣቶች የቢዝነስ ሃሳባቸውን ወደ ተግባር ለመለወጥ የሚያዳግታቸው መልከ ብዙ ተግዳሮቶች ይፈትኗቸዋል።

የሥራ ፈጠራ ሃሳባቸው ወደ ምርትና አገልግሎት ተቀይሮ ህልማቸውን ለመኖር ቢሹም የካፒታልና የመስሪያ ቦታ እጦት እንዲሁም ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት በማጣት የብዙ ወጣቶች ህልም ተጨናግፎ ይቀራል።

በአልባሳት ዲዛይን ሥራ ከልጅነቷ ጀምሮ ያደረባትን ፍላጎትና ህልም እውን ለማድረግ ከሚጥሩ ወጣቶች መካከል ሰሎሜ ክፍሉ ትጠቀሳለች።

የፈጠራ ሃሳብና የስራ ፍላጎት የሌሎች ድጋፍና እገዛ ከታከለበት ምን ያህል እንደሚያግዝ እኔ ጥሩ ምሳሌ መሆን እችላለሁ ትላለች።

የአልባሳት ዲዛይን ህልመኛዋ ሰሎሜ ሃሳቧን ሰንቃ ድጋፍና ምክር ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ፈጠራ ማዕከል በማማተሯ እገዛና ድጋፍ ተደርጎላት እቅዷ ተሳክቷል።

ወጣቷ ሰሎሜ ክፍሉ አሁን ላይ የሻዴዝ ዌር ክሎዚንግ ካምፓኒ መስራች በመሆን ከራሷ አልፋ ለሌሎች የሥራ እድል ፈጥራለች።

በአልባሳት፣ በቆዳ ውጤቶችና በዲጂታል አርት ስኬታማ በመሆን ምርቶቿን ለገበያ በማቅረብ ላይ ትገኛለች።

የፋሽን ዲዛይን ሙያ ላይ የተሰማራችው ወጣት ሳራ ንጉሴ፤ ከኢትዮጵያ ፈጠራ ማዕከል ያገኘችው እውቀት እርሷንም ለስኬት አብቅቷታል።

የኢትዮጵያ ፈጠራ ማዕከል ዲዛይነሮችን፣ ጥቃቅንና አነስተኛ አምራቾችን፣ ሥራ ፈጣሪዎችን በማብቃት ተወዳዳሪ ምርቶችን እንዲያቀርቡ የሚያስችል ተቋም ነው።

ማዕከሉ በተለይም ለወጣቶች በገበያ ጥናት ክህሎት፣ የንግድና የዲዛይን ሥራ ሥልጠና እንዲሁም የማማከር አገልግሎት ይሰጣል።

በዚህም ምክንያት ወጣት ሰሎሜ እና ሳራ የስኬት መንገድን መከተል መቻላቸውን የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ ተመስገን ፍስሐ ገልጸዋል።

በማዕከሉ የጋራ መሥሪያ ቦታ፣ የሥልጠና ወርክሾፕ፣ ላቦራቶሪ፣ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በማቅረብ ወጣቶች በሥራዎቻቸው ውጤታማና ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በማዕከሉ አሁን ላይ 173 የአምራች ኩባንያ አባላት አገልግሎቱን እያገኙ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ብሩ ወልዴ በበኩላቸው፤ የፈጠራ ማዕከሉ በአፍሪካ ከግብጽ በመቀጠል የሚጠቀስ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ማዕከሉ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ በየጊዜው አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በክልሎችም ተደራሽነቱን የማስፋት እድል ቢኖረው ሲሉ ጠቁመዋል።

የተለያዩ የቆዳና አልባሳት ውጤቶችን በማዘመን በስፋትና በጥራት በአገር ውስጥ እንዲመረት በማድረግ የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት፣ እንዲሁም በዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ነው የገለጹት።

በተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት እና በጣልያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ አማካኝነት የማዕከሉ ግንባታ እውን መሆኑ ታውቋል።

ለግንባታውና ለተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ 600 ሺህ ዩሮ ወጪ የተደረገበትን ማዕከል ባሳለፍነው ሳምንት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የጣልያን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማሪና ሴሬኒ መጎብኘታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም