ዓለም አቀፉን የምጣኔ ሃብት ቀውስ ለመቋቋም ኢትዮጵያ በግብርና፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቁጠባ ላይ ማተኮር አለባት - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፉን የምጣኔ ሃብት ቀውስ ለመቋቋም ኢትዮጵያ በግብርና፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቁጠባ ላይ ማተኮር አለባት
አዲስ አበባ መጋቢት 01/2014(ኢዜአ) በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የተፈጠረውን ዓለም አቀፍ የምጣኔ ሃብት ቀውስ ለመቋቋም ኢትዮጵያ በግብርና፣ በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትና በቁጠባ ላይ ማተኮር እንዳለባት አንድ ዓለም አቀፍ ቢዝነስ አማካሪ ተናገሩ።
ከተጀመረ ሁለት ሳምንታት ያስቆጠረው የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከወታደራዊነቱ ውጊያ ባለፈ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የኢነርጂ ፍልሚያን ያካተተ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ዓለም አቀፍ የቢዝነስ አማካሪው ዶክተር አህመድ አብዱራህማን ይገልጻሉ።
በሁለቱ አገሮች መካከል እየተካረረ የመጣው ጦርነት በተለይም የዓለምን የኢኮኖሚ ቀውስ አባብሶታል ብለዋል።
ለዓለም ገበያ 30 በመቶ የስንዴ ምርት በምታቀርበው ሩሲያ እና በስንዴ ምርት አቅርቦት የምትጠቀሰው ዩክሬን ወደ ጦርነት መግባታቸው በተለይም የምግብ እህል ግብይቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት።
የበቆሎ ምርትን ለዓለም ገበያ ከሚያቀርቡት ሀገራት ሩሲያ 19 በመቶውን እንደምትሸፍን ያነሱት ዶክተር አህመድ፤ የዓለምን የሱፍ ዘይት ገበያ አብዛኛውን ድርሻ የተቆጣጠሩትም ሩሲያና ዩክሬን መሆናቸውን አብራርተዋል።
ከዓለም አቀፍ የግብይት ቋቶች ባገኘነው መረጃ መሰረት ዩክሬን ለዓለም ገበያ ከ46 በመቶ በላይ፣ ሩሲያም ከ25 በመቶ ያላነሰ የሱፍ ዘይት ያቀርባሉ።
በየቀኑ ሩሲያ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ የነዳጅ ዘይትን ለዓለም ገበያ የምታቀርብ መሆኗ የዓለምን የነዳጅ ዘይት የገበያ ዋጋ በበርሜል ከነበረበት 80 ዶላር አሁን ወደ 140 ዶላር አድርሶታል።
ለግብርና ሥራ ዋነኛ ግብዓት የሆነውን ዩሪያና ዳፕ የተባለ የአፈር ማዳበሪያ የ15 በመቶ፣ ለቀይ አፈር የሚሆን ፖታሽ ማዳበሪያን ደግሞ 17 በመቶ የምታቀርበው ሩሲያ መሆኗን አንስተዋል።
ምርቶች ወደ ዓለም ገበያ እንዳይቀርቡ በሎጂስቲክስ ዘርፉ ላይ ጫና በመፍጠሩና የምርት ሂደትንም በማስተጓጎሉ በተለይም በማደግ ላይ ላሉ አገራት ትልቅ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ፈጥሯል ነው ያሉት።
የሁለቱ አገሮች ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ በተለይም የስንዴ ምርት አቅርቦት ላይ ጫና ይኖረዋል ብለዋል።
ሁለቱ አገሮች የሱፍ ዘይት በስፋት የሚመረትባቸው አገራት በመሆናቸው የሰሊጥና የኑግ ዘይት እጥረትና የዋጋ ንረት ፈጥሯል ነው ያሉት።
የዓለም ኢኮኖሚ እኤአ ከ2008 እስከ 2011 በቆየው የአሜሪካ የኢኮኖሚ ድቀት በኋላ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሌላ ፈተና መሆኑን አንስተዋል።
አሁን ላይ ደግሞ በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ዓለም ሌላ ፈተና ላይ ወድቋል ሲሉ ዶክተር አህመድ አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልከው በብዛት የግብርና ምርቶችን በመሆኑና የምርቶቹ አብዛኛው መዳረሻ አውሮፓ ከጥሬ እቃ ግብይት ይልቅ ጦርነቱ ላይ ትኩረት በማድረጋቸው የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ላይ ጫና ይኖረዋልም ነው ያሉት።
በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የሚሰጠውን የፋይናንስ ድጋፍ ለጦርነት ተፈናቃዮችና መልሶ ማቋቋሚያ በማዋል ታዳጊ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኙ ሊያደርግ እንደሚችልም ጠቁመዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ ጦርነቱ ያስከተለውን ዓለም አቀፋዊ ጫና ለመቋቋም የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይ በስፋት መስራት አለባት ብለዋል።
በተለይም ከጦርነቱ ቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውና በኢትዮጵያ ሰፊ ኢንቨስትመንት ካላቸው ቱርክ እና ቻይና ጋር ያለውን የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በተለይም በከተማ ግብርና ሁሉም ቤተሰብ አተኩሮ እንዲሰራና መንግስት እየወሰዳቸው ካሉ እርምጃዎች ባሻገር ኢትዮጵያዊያን በአንድ ልብ በትጋት ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት።
መንግስት በፖሊሲ ደረጃ ከውጭ የሚገባ የስንዴ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመሸፈን እየተገበረው ያለው የበጋ መስኖ ልማትን ማጠናከርም ሌላኛው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የጦርነቱ ጫና ለኢትዮጵያም ፈታኝ በመሆኑ ችግሩን በትብብርና አንድነት ለመሻገር ህዝብና መንግስት እጅ እና ጓንት ሆነው መስራት አለባቸው ብለዋል።
የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም የመንግስት አስተዳደር እና ህዝቡ በጋራ የሚቆሙበት ወሳኝ ወቅት ላይ እንገኛለን ያሉት ዶክተር አህመድ፤ ከነዳጅ ምርት ጀምሮ ወጪ ቁጠባ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ሲሉ መክረዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ህጋዊ በሆነ መልኩ ገንዘባቸውን ወደ አገር ቤት በመላክ መንግስትና ህዝባቸውን ማገዝ አለባቸው ብለዋል።