በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 79 በርሜል ናፍጣ በቁጥጥር ስር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 79 በርሜል ናፍጣ በቁጥጥር ስር ዋለ
አምቦ ፤ መጋቢት 1/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጄሬ ወረዳ ኤጄሬ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ 79 በርሜል ናፍጣ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።
ነዳጁ የሰሌዳ ቁጥሩ 3-A 06119 ኢት በሆነ የጭነት ተሸከርካሪ በህገ ወጥ መንገድ ከመናገሻ ኮሎቦ ወደ አሶሳ ለመውሰድ ታስቦ ሲጓጓዝ እንደተገኘ የኤጄሬ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጂን ሃይሉ ደቻሳ ገልጸዋል።
በ79 በርሜል ውስጥ 15 ሺህ 800 ሊትር የሆነው ናፍጣው መቆጣጠር የተቻለው ትናንት ኤጄሬ ኬላ ላይ በተደረገ ፍተሻ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
ነዳጁን ሲያጓጉዝ የነበረው አሽከርካሪው ለጊዜው ከአካባቢው ሸሽቶ ቢያመልጥም ለመያዝ ፖሊስ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ዋና ሳጂን ደቻሳ ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በህገ ወጥ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ነዳጅና ሌሎች ምርቶችን ለመቆጣጠር ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ላይ ኢትዮጵያ የምታስገባውን ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገር እንደሚወጣ መግለጻቸው ይታወሳል።
የአካባቢው አስተዳደር አካላትም በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ጎረቤት ሀገር የሚጓጓዘውን ነዳጅ ከነተሽከርካሪው እንዲወርሱ ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወቃል።