የአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድኦ ድርጅት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በአፋር ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ ተመለከቱ

125

መጋቢት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሜሪካ መንግስት የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩ. ኤስ. አይ. ዲ) ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ተፈናቅለው በኮሪ ወረዳ "ጉያህ" መጠለያ ጣቢያ የተጠለሉ ወገኖች ያሉበትን ሁኔታ ዛሬ ተመለከቱ።

የዩ. ኤስ. አይ. ዲ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች የአደጋ ፈጣን ምላሽ ቡድንን ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል።

የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ተወካይ አቶ ማሄ አሊ ለድርጅቱ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ማሄ በማብራሪያቸው እንደገለጹት በሽቡር ቡድኑ ወረራ ምክንያት በክልሉ በ21 ወረዳዎች የሚገኙ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሰዎች ለአስቸኳይ ምግብ እርዳታ ጠባቂነት ተዳርገዋል።

"ከተጎጂዎች መካከል ከ600 ሺህ በላይ የሚሆኑት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ" ብለዋል ።

ከተፈናቀሉት ውስጥም በቅርቡ በቂልበቲ-ረሱ ዞን በሽብር ቡድኑ በአምስት ወረዳዎች በተፈጸመ ወረራ ተፈናቅለው በ14 መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ 294 ሺህ ሰዎች ሰብአዊ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን አብራርተዋል።

በኩሪ ወረዳ የጉያህ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች ጨምሮ ከአበአላ፣ በራህሌና ኩነባ ወረዳዎች የተፈናቀሉ አባወራዎች የዚሁ አካል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስት ከተለያዩ ተባባሪ አካላት ጋር በመሆን ለተፈናቃዮች ምግብና አስፈላጊ ድጋፎችን እንዲሁም መጠሊያዎችን እያቀረበ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አኳያ ብዙ ቀሪ ስራ መኖሩን አመልክተዋል።

"በተለይም የመጠለያው የእናቶችና ህጻናት አልሚ ምግብና የህክምና አገልግሎት ፍላጎትን ለማሻሻል እንደ ዩ.ኤስ.አይ.ዲ አይነት አጋር አካላት ንቁ ተሳትፎ ይጠይቃል" ብለዋል።

የአሜሪካን መንግስት የልማት ተራድኦ ድርጅት የስራ ሃላፊዎች ጉብኝት በተጨባጭ ህብረተሰቡ ያለበትን ሁኔታ በመገንዘብ በቀጣይ ክፍተቶችን በመለየት አስፈላጊውን ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ አቶ ማሄ በማብራሪያቸው አስታውቀዋል።

ከኩነባ ወረዳ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያው የተጠለሉ አቶ እድሪስ አደም በበኩላቸው "መንግስት የሚችለውን ያክል የመጠለያና የምግብ ድጋፍ እያደረገልን ቢሆንም ዋነኛ የኑሯችን መሰረት የሆኑ የቤት እንስሳቶች ጨምሮ ሙሉ ንብረታችንን ጥለን የተፈናቀልን በመሆኑ ተቸግረናል" ሲሉ ገልጸዋል።

"በተለይም የሚያጠቡ ሴቶች ጨምሮ ህጻናት የተለያዩ ምግብና ተያያዥ ቁሳቁሶች ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል" ብለዋል።

ከአበአላ ወረዳ የተፈናቀሉ ወይዘሮ ፉጡማ አብደላ "በመጠለያ ጣቢያው የምንገኝ ተፈናቃዩች ቢያንስ ህይወታችንን ለማቆየት የሚያስችል ድጋፍ እያገኘን ነው" ብለዋል።

ከችግሩ ስፋት አኳያ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም