ፓርቲው እራሱን ፈትሾ የሀገሪቱን አንገብጋቢ ችግሮች ለመፍትት የሚያስችል አቅጣጫ ማስቀመጥ ይኖርበታል- ምሁራን

144

ሀዋሳ የካቲት 30/2014 (ኢዜአ)የብልጽገና ፓርቲ መስራች ጉባዔ ፓርቲው እራሱን በሚገባ ፈትሾ የሀገሪቱን አንድነት ለማጠናከርና የህዝቡን አንገብጋቢ መሠረታዊ ችግሮች ለመፍትት የሚያስችል አቅጣጫ መስቀመጥ ይኖርበታል ይላሉ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ።

በዩኒቨርስቲው የማህበራዊ ሣይንስና ሥነ ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዳኜ ሽብሩ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የህዝብ ይሁንታ አግኝቶ ለስልጣን የበቃው ብልጽግና የህግ የበላይነትን ለማረጋጋጥ ፣ ሠላም ለማስፈን፣  የዜጎችን መብት ለማስከበርና የዜጎችን  ኑሮ ለማሻሻል  ቃል ገብቷል።

በተለይ ፓርቲው በኢትዮጵያ ህዝብ ለውጥ ፍላጎት ሀገሪቷን ከተጋረጠባት አደጋ ለማሻገር የሚያስችል  እሳቤ ይዞ የመጣ በመሆኑ እሳቸውን ጨምሮ በህዝብ ዘንድ ትልቅ ተስፋ እንደጣሉበት ነው ው ያመለከቱት።

ባለፉት ሶስት ዓመታት ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በመቅረጽና በመተግብር፣የህዝብ አንድነትን በማምጣት  ያስመዘገበው ተስፋ ሰጭ ውጤት በህዝቡ ዘንድ ይሁንታ አግኝቶ እንዲመረጥ ማስቻሉን ጠቅሰዋል።

ሆኖም አሁን ላይ ሀገሪቱ ከተጋረጡባት ተግዳራቶች አንፃር በቀጣይ ብዙ የቤት  ሥራ እንደሚጠብቀው አብራርተዋል።

እነዚህን የቤት ስራዎችን ለመፍታት  እና እራሱን ለመፈተሽ ብልዕግና አሁን የሚያካሂደው ጉባዔ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርለት ገልጸው በተለይ አሁን ለተንሰራፈው የኑሮ ውድነት እልባት ለማበጀትና የዘረኝነት አባዜም መልክ የሚያሲዝ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብዬ ነው የማስበው ብለዋል።

እንደበፊቱ  የፖርቲው አባላት ተሰባስበው አቅጣጫ አስቀምጠናል ብለው የሚለያዩ ከሆነ ትርጉም የለውም ያሉት ዶክተር ዳኜ ፤ ይልቁንም የዜጎች አንገብጋቢ ጉዳዮችን በዝርዝር እና በጥልቀት በመፈተሽና በመገምገም ተግባራዊ የሚሆኑ ስራዎች ተለይተው ሊቀመጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በዘመነ ኢህአዴግ የተለመዱ አካሄዶች አሁን መቆም አለባቸው  ያሉት ዶክተር ዳኜ ፤በዚህ ጉባዔ ፓርቲው የሚፈጽመውን ውጥኖች ነቅሶ አንድ በአንድ በማስቀመጥ ማሳየት መቻል እንዳለበት ነው የገለጹት።

በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖር በትክክል የማይሰሩ፣በጎሰኝነትና ብሄር የተተበተቡ አመራሮችን በግምገማ በማጥራት ፓርቲው በቃ ሊለቻው እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት ዜጎችን በከፍተኛ ደረጃ እየተፈታተነ ላለው የሸቀጦች ዋጋ ንረት ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆን መስተካከል በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ጉባኤው ተወያይቶ መፍትሄ  ያስቀምጣል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንዲቻል ሊካሄደው የታሰበው ብሄራዊ ምክክር በስኬት እንዲጠናቀቅ ሰዎች የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይዙ  ፓርቲው በየደረጃው ግልጽነት እንዲፈጠር መስራት እንደሚኖርበትም አመልክተዋል።

በዩኒቨርስቲው የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዳይሬክተር ዮሐናን ዮካሞ በበኩላቸው ፤ ከጉባዔው በፓርቲው  የሚመራ ጠንካራ መንግሥት ሥርዓት፣  በየደረጃው አሳታፊና ቀልጣፋ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ያደረገ ታሪካዊ ውሳኔዎችን እንደሚጠበቁ ተናግረዋል።

ሀገሪቷ ያላትን የማደግና የመበልጸግ ተስፋ እውን ለማድረግ እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በከፍተኛ ደረጃ ለማልማት የሚያስችል አቅጣጫ ጉባዔው እንደሚያስቀምጥ እምነቴ ነው ብለዋል።

እንዲሁም ጉባዔው የሀገሪቱን ሠላም፣ አንድነትና ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር፣ በሂደቱ የነበሩ ጥንካሬዎች አጎልብቶ ለመቀጠልና  ጉድለቶችን ነቅሶ በማውጣት የተሻለ አቅጣጫ ይይዛል ብለው እንደሚጠብቁ ገልፀዋል።

ምንም እንኳ ፓርቲው የራሱ የውስጥ አሰራሮች ቢኖረውም ሀገሪቱ ላጋጠማት የተለያዩ ችግሮች ዘለቄታዊ ለውጥ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እንዲመጣ ብልዕግና የሚመራው መንግሥት አበክሮ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ፓርቲው ህዝብ የሰጠውን ይሁንታ ወደ እድል ቀይሮ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የህዝቦችን የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ የዜጎች ደህንነትና ሰላም እንዲሁም የተጀመረውን የህዳሴ ጉዞ ወደ አንድ ታሪካዊ ምዕራፍ የሚያሽጋግሩ አቅጣጫዎች የሚያስቀምጥ የተሳካ ጉባዔ እንደሚሆን  ዳይሬክተሩ ያላቸውን ተስፋ  ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም